22 በኔጌብ በኩል አልፈው አኪመን፣ ሴሲና ተላሚ የተባሉ የዔናቅ ዝርያዎች ወደሚኖሩበት ወደ ኬብሮን መጡ። ኬብሮን የተመሠረተችው ጣኔዎስ በግብፅ ምድር ከመቈርቈሯ ሰባት ዓመት አስቀድሞ ነበር።
23 ወደ ኤሽኮል ሸለቆ በደረሱ ጊዜ የወይን ዘለላ ያንዠረገገ አንድ ቅርንጫፍ ቈረጡ፤ ይህንንም ከሮማንና ከበለስ ጋር በመሎጊያ አድርገው ለሁለት ተሸከሙት።
24 እስራኤላውያን የወይን ዘለላ ስለ ቈረጡባትም ያች ስፍራ የኤሽኮል ሸለቆ ተባለች።
25 ምድሪቱንም አሥሠው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ።
26 ሰዎቹም፣ ሙሴና አሮን መላውም የእስራኤላውያን ማኅብረ ሰብ ወዳሉበት በፋራን ምድረ በዳ ወደምትገኘው ወደ ቃዴስ ተመለሱ፤ ያዩትንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ አስረዱ፤ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው።
27 ለሙሴም እንዲህ ብለው ነገሩት፤ “ወደ ላክኸን ምድር ዘልቀን ገባን፤ ማርና ወተት የምታፈስስ ናት፤ ፍሬዋም ይኸው።
28 በዚያ የሚኖሩት ሰዎች ግን ኀያላን ሲሆኑ፣ ከተሞቹም የተመሸጉና ትላልቅ ናቸው፤ እንዲያውም የዔናቅን ዝርያዎች በዚያ አይተናል።