ዘኁልቍ 32:11-17 NASV

11 ‘በፍጹም ልባቸው ስላልተከተሉኝ ከግብፅ ከወጡት፣ ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች አንዳቸውም ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ልሰጥ በመሐላ ቃል የገባሁላቸውን ምድር አያዩዋትም፤

12 እግዚአብሔርን (ያህዌ) በፍጹም ልባቸው ተከትለውታልና፣ ከቄኔዛዊው ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በስተቀር አንዳቸውም አያዩዋትም።’

13 የእግዚአብሔርም (ያህዌ) ቊጣ በእስራኤል ላይ ስለ ነደደ፣ በፊቱ ክፉ ነገር ያደረገው ያ ትውልድ በሙሉ እስኪያልቅ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ አደረጋቸው።

14 “እናንት የኀጢአተኞች ልጆች ይኸው በአባቶቻችሁ እግር ተተክታችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤል ላይ ይበልጥ እንዲቈጣ ታደርጋላችሁ።

15 እርሱን ከመከተል ብትመለሱ አሁንም ይህን ሁሉ ሕዝብ በምድረ በዳ ይተወዋል፤ ለሚደርስበትም ጥፋት ምክንያቱ እናንተው ትሆናላችሁ።”

16 ከዚህ በኋላ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፤ “እዚህ ለከብቶቻችን በረቶች፣ ለሴቶቻችንና ለልጆቻችን ከተሞች መሥራት እንወዳለን፤

17 ይሁን እንጂ ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ ታጥቀንና በእስራኤላውያን ፊት ግንባር ቀደም ሆነን ለመሄድ ዝግጁ ነን፤ በዚህም ጊዜ ሴቶቻችንና ልጆቻችን በምድሪቱ ላይ ካሉት ነዋሪዎች እንዲጠበቁ በተመሸጉ ከተሞች ይኖራሉ።