1 ከዮሴፍ ዝርያ ጐሣዎች የሆኑ የምናሴ ልጅ፣ የማኪር ልጅ፣ የገለዓድ ጐሣ የቤተ ሰብ አለቆች ወደ ሙሴና የእስራኤላውያን ቤተ ሰቦች አለቆች ወደሆኑት መሪዎች ቀርበው ተናገሩ፤
2 እንዲህም አሉ፤ “ምድሪቱን በዕጣ ከፋፍለህ ለእስራኤላውያን ርስት አድርገህ እንድትሰጣቸው እግዚአብሔር (ያህዌ) አንተን ጌታዬን ባዘዘ ጊዜ የወንድማችንን የሰለጰዓድን ድርሻ ለሴቶች ልጆቹ እንድትሰጥ አዞሃል።
3 ከሌሎች የእስራኤል ነገዶች ባል ቢያገቡ ድርሻቸው ከእኛ የዘር ርስት ላይ ተወስዶ የሚያገቧቸው ሰዎች ላሉበት ነገድ ይተላለፋል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ በዕጣ ከተደለደለልን ርስት ላይ ከፊሉ ሊቀነስብን ነው።
4 የእስራኤላውያን ዓመተ ኢዮቤልዩ በሚመጣበት ጊዜ የእነርሱ ድርሻ ወደ ባሎቻቸው ነገድ ይጨመራል፤ ይህ ከሆነም ድርሻቸው ከአባቶቻችን ነገድ ርስት ላይ ይወሰዳል።”