ኢሳይያስ 49:18-24 NASV

18 ዐይንሽን ቀና አድርጊ፤ ዙሪያውንም ተመልከቺ፤ወንዶች ልጆችሽ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ።“በሕያውነቴ እምላለሁ፤እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፤እንደ ሙሽራም ትጐናጸፊያቸዋለሽ” ይላል እግዚአብሔር።

19 “ፈራርሰሽ ባድማ ብትሆኚ፣ምድርሽ ፈጽሞ ቢጠፋ፣ዛሬ ለሕዝብሽ ጠባብ ብትሆኚም እንኳ፣የዋጡሽ ከአንቺ ይርቃሉ።

20 በሐዘንሽ ዘመን የወለድሻቸው ልጆች፣ጆሮሽ እየሰማ፣‘ይህ ቦታ በጣም ጠቦናል፤የምንኖርበት በቂ ስፍራ ስጪን’ ይሉሻል።

21 በልብሽም እንዲህ ትያለሽ፣‘እነዚህን የወለደልኝ ማን ነው?እኔ ሐዘንተኛና መካን፣የተሰደድሁና የተጠላሁ ነበርሁ፤እነዚህን ማን አሳደጋቸው?ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ታዲያ፣ እነዚህ ከየት መጡ?’

22 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እነሆ፤ አሕዛብን በጥቅሻ እጣራለሁ፤ዐርማዬንም ለሕዝቦች ከፍ አደርጋለሁ፤ወንዶች ልጆችሽን በዕቅፋቸው ያመጡልሻል፤ሴቶች ልጆችሽንም በትከሻቸው ይሸከሙልሻል።

23 ነገሥታት አሳዳጊ አባቶችሽ፣እቴጌዎቻቸው ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤በግንባራቸው ተደፍተው ይሰግዱልሻል፤የእግርሽን ትቢያ ይልሳሉ፤አንቺም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቂያለሽ፤እኔን ተስፋ የሚያደርጉም አያፍሩም።”

24 ከተዋጊ ብዝበዛ ማስጣል፣ከጨካኝስ ምርኮኞችን ማዳን ይቻላልን?