ኢሳይያስ 49:7-13 NASV

7 እግዚአብሔር፣ታዳጊ የሆነው የእስራኤል ቅዱስ፣ለተናቀውና በሕዝብ ለተጠላው፣የገዦች አገልጋይ እንዲህ ይላል፤“ነገሥታት አይተውህ ይነሣሉ፤ልዑላንም አይተው፤ ይሰግዳሉ፤ምክንያቱም የመረጠህ የእስራኤል ቅዱስ፣ እግዚአብሔር ታማኝ ነው።”

8 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በወደድሁ ጊዜ እመልስልሃለሁ፤በድነትም ቀን እረዳሃለሁ።ለሕዝቡ ቃል ኪዳን እንድትሆን፣ምድሪቱን እንደ ገና እንድትሠራት፣ጠፍ የሆኑትን ርስቶች ለየባለቤታቸው እንድትመልስ፣እጠብቅሃለሁ፤ እሠራሃለሁም፤

9 የተማረኩትን፣ ‘ኑ ውጡ’በጨለማ ያሉትን፣ ‘ነጻ ሁኑ’ እንድትል አድርጌሃለሁ።“በየመንገዱ ዳር ይመገባሉ፤በተራቈተውም ኰረብታ ሁሉ ላይ መሰማሪያ ያገኛሉ።

10 አይራቡም፤ አይጠሙም፤የምድረ በዳ ትኵሳት ወይም የፀሓይ ቃጠሎ አይጐዳቸውም።የሚራራላቸው ይመራቸዋል፤በውሃ ምንጭ ዳርም ያሰማራቸዋል።

11 ተራሮቼን ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፤ጐዳናዎቼም ከፍ ይላሉ።

12 እነሆ፤ ከሩቅ አገር ይመጣሉ፤አንዳንዶች ከሰሜን ሌሎች ከምዕራብ፣የቀሩት ደግሞ ከሲኒም ይመጣሉ።

13 ሰማያት ሆይ፤ እልል በሉ፤ምድር ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤ተራሮች ሆይ፤ በደስታ ዘምሩ፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ያጽናናል፤ለተቸገሩትም ይራራልና።