5 ጽድቄ በፍጥነት እየቀረበ፣ማዳኔም እየደረሰ ነው፤ክንዴም ለመንግሥታት ፍትሕን ያመጣል፤ደሴቶች ወደ እኔ ይመለከታሉ፤ክንዴንም በተስፋ ይጠብቃሉ።
6 ዐይኖቻችሁን ወደ ሰማያት አንሡ፤ወደ ታች ወደ ምድርም ተመልከቱ፤ሰማያት እንደ ጢስ በነው ይጠፋሉ፤ምድር እንደ ልብስ ታረጃለች፤ነዋሪዎቿም እንደ አሸን ፈጥነው ይረግፋሉ፤ማዳኔ ግን ለዘላለም ይኖራል፤ጽድቄም መጨረሻ የለውም።
7 “እናንት ጽድቅን የምታውቁ፣ሕጌንም በልባችሁ ያኖራችሁ ሰዎች ስሙኝ፤ሰዎች ሲዘብቱባችሁ አትፍሩ፤ሲሰድቧችሁ አትደንግጡ።
8 ብል እንደ ልብስ ይበላቸዋል፤ትል እንደ በግ ጠጒር ይውጣቸዋል፤ጽድቄ ግን ለዘላለም፣ማዳኔም ከትውልድ እስከ ትውልድ ጸንታ ትኖራለች።”
9 የእግዚአብሔር ክንድ ሆይ፤ተነሥ፤ ተነሥ! ኀይልን ልበስ፤እንዳለፉት ዘመናት፣በጥንት ትውልዶችም እንደሆነው ሁሉ ተነሥ።ረዓብን የቈራረጥህ፣ታላቁን ዘንዶ የወጋህ አንተ አይደለህምን?
10 የዳኑት እንዲሻገሩ ባሕሩን፣የታላቁን ጥልቅ ውሆች ያደረቅህ፣በጥልቁም ውስጥ መንገድ ያበጀህ፣አንተ አይደለህምን?
11 እግዚአብሔር የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤በዝማሬ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤የዘላለማዊ ደስታን አክሊል ይቀዳጃሉ፤ተድላና ደስታ ያገኛሉ፤ሐዘንና ልቅሶም ከእነርሱ ይሸሻል።