1 ከዚህ በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ሞተ፤ ልጁ ሐኖንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
2 ዳዊትም፣ “አባቱ ቸርነትን እንዳደረገልኝ ሁሉ፣ እኔም ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ወሮታውን ልክፈል” ሲል አሰበ። ስለዚህ ስለ አባቱ ሞት የተሰማውን ሐዘን እንዲገልጹለት ዳዊት መልክተኞችን ላከ።የዳዊት ሰዎች ወደ አሞናውያን ምድር በደረሱ ጊዜ፣
3 የአሞናውያን መኳንንት ጌታቸውን ሐኖንን፣ “ዳዊት የተሰማውን ሐዘን ለመግለጽ ሰዎች መላኩ አባትህን ለማክበር አስቦ ይመስልሃል? የላካቸው ሰዎች ከተማዪቱን እንዲመረምሩ፣ እንዲሰልሉና እንዲያጠፏት አይደለምን?” አሉት።
4 ስለዚህ ሐኖን የዳዊትን ሰዎች ይዞ፣ የእያንዳንዳቸውን ጢም በከፊል ላጨ፣ ልብሳቸውንም ወገባቸው ድረስ አሳጥሮ በመቍረጥ መልሶ ሰደዳቸው።
5 ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፣ ሰዎቹ እጅግ ዐፍረው ስለ ነበር መልክተኞቹን ላከባቸው፤ ንጉሡም፣ “ጢማችሁ እስኪያድግ በኢያሪኮ ቈዩና ከዚያ በኋላ ተመለሱ” አላቸው።