2 ሳሙኤል 10:1-6 NASV

1 ከዚህ በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ሞተ፤ ልጁ ሐኖንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

2 ዳዊትም፣ “አባቱ ቸርነትን እንዳደረገልኝ ሁሉ፣ እኔም ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ወሮታውን ልክፈል” ሲል አሰበ። ስለዚህ ስለ አባቱ ሞት የተሰማውን ሐዘን እንዲገልጹለት ዳዊት መልክተኞችን ላከ።የዳዊት ሰዎች ወደ አሞናውያን ምድር በደረሱ ጊዜ፣

3 የአሞናውያን መኳንንት ጌታቸውን ሐኖንን፣ “ዳዊት የተሰማውን ሐዘን ለመግለጽ ሰዎች መላኩ አባትህን ለማክበር አስቦ ይመስልሃል? የላካቸው ሰዎች ከተማዪቱን እንዲመረምሩ፣ እንዲሰልሉና እንዲያጠፏት አይደለምን?” አሉት።

4 ስለዚህ ሐኖን የዳዊትን ሰዎች ይዞ፣ የእያንዳንዳቸውን ጢም በከፊል ላጨ፣ ልብሳቸውንም ወገባቸው ድረስ አሳጥሮ በመቍረጥ መልሶ ሰደዳቸው።

5 ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፣ ሰዎቹ እጅግ ዐፍረው ስለ ነበር መልክተኞቹን ላከባቸው፤ ንጉሡም፣ “ጢማችሁ እስኪያድግ በኢያሪኮ ቈዩና ከዚያ በኋላ ተመለሱ” አላቸው።

6 አሞናውያን፣ ዳዊት እንደ ጠላቸው ባወቁ ጊዜ፣ ከቤትሮዖብና ከሱባ ሃያ ሺህ ሶርያውያን እግረኛ ወታደሮችን እንዲሁም ንጉሥ መዓካን ከአንድ ሺህ ሰዎቹ ጋር ደግሞም ከጦብ ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ቀጠሩ።