2 ሳሙኤል
ምዕራፎች 10:3-9
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
3የአሞናውያን መኳንንት ጌታቸውን ሐኖንን፣ “ዳዊት የተሰማውን ሐዘን ለመግለጽ ሰዎች መላኩ አባትህን ለማክበር አስቦ ይመስልሃል? የላካቸው ሰዎች ከተማዪቱን እንዲመረምሩ፣ እንዲሰልሉና እንዲያጠፏት አይደለምን?” አሉት።
4ስለዚህ ሐኖን የዳዊትን ሰዎች ይዞ፣ የእያንዳንዳቸውን ጢም በከፊል ላጨ፣ ልብሳቸውንም ወገባቸው ድረስ አሳጥሮ በመቍረጥ መልሶ ሰደዳቸው።
5ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፣ ሰዎቹ እጅግ ዐፍረው ስለ ነበር መልክተኞቹን ላከባቸው፤ ንጉሡም፣ “ጢማችሁ እስኪያድግ በኢያሪኮ ቈዩና ከዚያ በኋላ ተመለሱ” አላቸው።
6አሞናውያን፣ ዳዊት እንደ ጠላቸው ባወቁ ጊዜ፣ ከቤትሮዖብና ከሱባ ሃያ ሺህ ሶርያውያን እግረኛ ወታደሮችን እንዲሁም ንጉሥ መዓካን ከአንድ ሺህ ሰዎቹ ጋር ደግሞም ከጦብ ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ቀጠሩ።
7ዳዊት ይህን ሲሰማ፣ ኢዮአብን ከመላው ተዋጊ ሰራዊት ጋር ላከው።
8አሞናውያን ወጥተው በከተማቸው መግቢያ በር ላይ ተሰለፉ፤ የሱባና የረአብ ሶርያውያን እንዲሁም የጦብና የመዓካ ሰዎች ለብቻ ሜዳው ላይ ተሰለፉ።
9ኢዮአብም ከፊትና ከኋላው ጦር እንደ ከበበው ባየ ጊዜ፣ በእስራኤል ጀግንነታቸው ከታወቀው ጥቂቶቹን መርጦ በሶርያውያን ግንባር አሰለፋቸው።