2 ሳሙኤል 2:24-30 NASV

24 ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን ተከታተሉት፤ እያሳደዱም ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ከጋይ አጠገብ ወዳለው ወደ አማ ኰረብታ ሲደርሱ ፀሓይ ጠለቀች።

25 ከዚያም የብንያም ሰዎች ወደ አበኔር ተሰብስበው ግንባር በመፍጠር በኰረብታው ጫፍ ላይ ተሰለፉ።

26 አበኔር ኢዮአብን ጠርቶ፣ “ይህ ሰይፍ ዘላለም ማጥፋት አለበትን? ውጤቱ መራራ መሆኑን አንተስ ሳታውቀው ቀርተህ ነውን? ሰዎችህ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን እንዲያቆሙ ትእዛዝ የማትሰጣቸውስ እስከ መቼ ድረስ ነው?” አለው።

27 ኢዮአብም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ባትናገር ኖሮ፣ ሰዎቹ እስኪነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን ባላቆሙም ነበር” ብሎ መለሰ።

28 ስለዚህ ኢዮአብ ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ከዚያም በኋላ ሰዎቹ በሙሉ እስራኤልን ማሳደዱን ተው፤ ውጊያውም በዚሁ አበቃ።

29 አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ዓረባን አልፈው ሄዱ፤ ከዚያም ዮርዳኖስን በመሻገር ቢትሮንን ሁሉ ዐልፈው ወደ መሃናይም መጡ።

30 ከዚያም ኢዮአብ አበኔርን ማሳደዱን ትቶ ተመለሰ፤ ሰዎቹንም ሁሉ አንድ ላይ በሰበሰባቸው ጊዜ፣ ከዳዊት ሰዎች አሣሄልን ሳይጨምር፣ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች መጥፋታቸው ታወቀ።