1 እግዚአብሔር ለያዕቆብ ይራራለታል፤እስራኤልን እንደ ገና ይመርጠዋል፤በራሳቸውም አገር ያኖራቸዋል።መጻተኞች አብረዋቸው ይኖራሉ፤ከያዕቆብም ቤት ጋር ይተባበራሉ።
2 አሕዛብም ይወስዷቸዋል፤ወደ ገዛ ስፍራቸውም ይመልሷቸዋል።የእስራኤል ቤት አሕዛብን ርስት ያደርጓቸዋል፤ በእግዚአብሔርም ምድር ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች አድርገው ይገዟቸዋል፤የማረኳቸውን ይማርኳቸዋል፤የጨቈኗቸውንም ይገዟቸዋል።
3 እግዚአብሔር ከሥቃይህ፣ ከመከራህና ከጽኑ ባርነትህ ባሳረፈህ ቀን፣
4 በባቢሎን ንጉሥ ላይ ትሣለቃለህ፤ እንዲህም ትላለህ፤ጨቋኙ እንዴት አበቃለት!አስገባሪነቱስ እንዴት አከተመ!
5 እግዚአብሔር የክፉዎችን ዘንግ፣የገዦችንም በትረ መንግሥት ሰብሮአል፤
6 ሕዝቦችን በማያቋርጥ ቍጣ የመታውን፣ያለ ርኅራኄ እያሳደደየቀጠቀጠውን ሰብሮአል።