ኢሳይያስ 19:19-25 NASV

19 በዚያ ቀን በግብፅ ምድር መካከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራል፤ በድንበሯም ላይ ለእግዚአብሔር ዐምድ ይቆማል።

20 ይህም በግብፅ ምድር ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ምልክትና ምስክር ይሆናል፤ ከሚያስጨን ቋቸውም የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፣ አዳኝና ታዳጊ ይልክላቸዋል፤ እርሱም ያድናቸዋል።

21 እግዚአብሔር ራሱን ለግብፃውያን ይገልጣል፤ እነርሱም በዚያ ቀን እግዚአብሔርን ያውቁታል፤ በመሥዋዕትና በእህል ቍርባንም ያመልኩታል። ለእግዚአብሔር ስለት ይሳላሉ፤ የተሳሉትንም ይፈጽሙታል።

22 እግዚአብሔር ግብፅን በመቅሠፍት ይመታታል፤ መትቶም፤ ይፈውሳቸዋል። እነርሱም ወደ እግዚአብሔር ይመለሳሉ፤ እርሱም ልመናቸውን ሰምቶ ይፈውሳቸዋል።

23 በዚያ ቀን ከግብፅ ወደ አሦር አውራ መንገድ ይዘረጋል፤ አሦራውያን ወደ ግብፅ፣ ግብፃውያንም ወደ አሦር ይሄዳሉ፤ ግብፃውያንና አሦራውያን በአንድነት ያመልካሉ።

24 በዚያ ቀን እስራኤል፣ ከግብፅና ከአሦር ጋር የምድር በረከት ለመሆን በሦስተኛነት ትቈጠራለች።

25 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርም፣ “ሕዝቤ ግብፅ፣ የእጄ ሥራ አሦር፣ ርስቴም እስራኤል የተባረኩ ይሁኑ” ብሎ ይባርካቸዋል።