ኢሳይያስ 28:1-7 NASV

1 ለኤፍሬም ሰካራሞች የመታበያ አክሊል ለሆነች፣በለመለመ ሸለቆ ዐናት ላይ ጒብ ብላ፣የክብሩ ውበት ለሆነች ጠውላጋ አበባ፣የወይን ጠጅ ለዘራቸው መኵራሪያ ለሆነች፣ለዚያች ከተማ ወዮላት!

2 እነሆ፤ ጌታ ኀያልና ብርቱ የሆነ ነገር አለው፤ይህም እንደ በረዶ ወጀብ፣ እንደሚያጠፋ ዐውሎ ነፋስ፣እንደ ኀይለኛ ማዕበል፣ እንደ ከባድ ዝናብ፣በኀይል ወደ ምድር ይጥላታል።

3 የኤፍሬም ሰካራሞች የመታበያ አክሊል፣በእግር ይረገጣል።

4 በለምለሙ ሸለቆ ዐናት ላይ ጒብ ብላ፣የክብሩ ውበት የሆነች ጠውላጋ አበባ፣ከመከር በፊት እንደ ደረሰች፣ሰውም ድንገት አይቶ እንደሚቀጥፋትወዲያውኑም እንደሚውጣት በለስ ትሆናለች።

5 በዚያን ቀን የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ለተረፈው ሕዝቡ፣የክብር ዘውድ፣የውበትም አክሊል ይሆናል።

6 እርሱም በፍርድ ወንበር ላይ ለሚቀመጠው፣የፍትሕ መንፈስ፣ጦርን ከከተማዪቱ በር ላይ ለሚመልሱም፣የኀይል ምንጭ ይሆናል።

7 እነዚህም በወይን ጠጅ ይንገዳገዳሉ፤በሚያሰክርም መጠጥ ይወላገዳሉ፤ካህናቱና ነቢያቱ በሚያሰክር መጠጥ ተንገደገዱ፤በወይን ጠጅ ነገር ተምታታባቸው፤በሚያሰክር መጠጥ ተወላገዱ፤ራእይ ሲያዩ ይስታሉ፤ፍርድ ሲሰጡም ይሰናከላሉ።