7 የጋጠወጥ ዘዴ ክፉ ነው፤የችግረኛም አቤቱታ ትክክል ቢሆን፣ድኻን በሐሰት ለማጥፋት፣ክፋት ያውጠነጥናል።
8 ጨዋ ግን ሐሳቡም ጨዋ ነው፤በጨዋነት ምግባርም ጸንቶ ይገኛል።
9 እናንት ትዕቢት የወጠራችሁ ሴቶች፣ተነሡ፤ ድምፄን ስሙ፤እናንት ተደላድላችሁ የምትኖሩ፣ ሴቶች ልጆች ሆይ፤የምነግራችሁን አድምጡ።
10 ዓመቱ ገና እንዳለፈ፣ተደላድላችሁ የነበራችሁ ትንቀጠቀጣላችሁ፤የወይን ተክል ፍሬ አይሰጥም፤የፍራፍሬም ወቅት አይመጣም።
11 እናንት ትዕቢት የወጠራችሁ ሴቶች ተንቀጥቀጡ፤እናንት ተደላድላችሁ የምትኖሩ ሴቶች ልጆች፤ በፍርሀት ተርበትበቱ፤ልብሳችሁን አውልቁ፣ወገባችሁን በማቅ ታጠቁ።
12 ስለ ለሙ መሬት ደረታችሁን ምቱ፤ስለ ፍሬያማው የወይን ተክል ዕዘኑ፤
13 ስለ ሕዝቤ ምድር፣እሾኽና አሜከላ ስለ በቀለበት ምድር፣ስለ ፈንጠዝያ ቤቶች ሁሉ፣ስለዚህችም መፈንጫ ከተማ አልቅሱ።