9 እናንት ትዕቢት የወጠራችሁ ሴቶች፣ተነሡ፤ ድምፄን ስሙ፤እናንት ተደላድላችሁ የምትኖሩ፣ ሴቶች ልጆች ሆይ፤የምነግራችሁን አድምጡ።
10 ዓመቱ ገና እንዳለፈ፣ተደላድላችሁ የነበራችሁ ትንቀጠቀጣላችሁ፤የወይን ተክል ፍሬ አይሰጥም፤የፍራፍሬም ወቅት አይመጣም።
11 እናንት ትዕቢት የወጠራችሁ ሴቶች ተንቀጥቀጡ፤እናንት ተደላድላችሁ የምትኖሩ ሴቶች ልጆች፤ በፍርሀት ተርበትበቱ፤ልብሳችሁን አውልቁ፣ወገባችሁን በማቅ ታጠቁ።
12 ስለ ለሙ መሬት ደረታችሁን ምቱ፤ስለ ፍሬያማው የወይን ተክል ዕዘኑ፤
13 ስለ ሕዝቤ ምድር፣እሾኽና አሜከላ ስለ በቀለበት ምድር፣ስለ ፈንጠዝያ ቤቶች ሁሉ፣ስለዚህችም መፈንጫ ከተማ አልቅሱ።
14 ዐምባ ምሽጉ ወና ይሆናል፤ውካታ የበዛበት ከተማ ጭር ይላል፤ምሽጉና ማማው ለዘላለሙ ዋሻ፣የዱር አህያ መፈንጫ፣ የመንጋም መሰማሪያ ይሆናል፤
15 ይህም የሚሆነው መንፈስ ከላይ እስኪፈስልን፣ምድረ በዳው ለም መሬት፣ለሙ መሬትም ጫካ እስኪመስል ድረስ ነው።