ኢሳይያስ 37:1-7 NASV

1 ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን ሲሰማ፣ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለበሰ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገባ።

2 የቤተ መንግሥቱን አስተዳዳሪ ኤልያቄምንና ጸሓፊውን ሳምናስን እንዲሁም ከካህናቱ ዋና ዋናዎቹን ማቅ ለብሰው ሁሉም ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ላካቸው።

3 እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፤ ይህ ቀን የጭንቀት፣ የተግሣጽና የውርደት ቀን ነው፤ ሕፃናት ሊወለዱ ሲሉ ብርታት እንደሚታጣበት ቀን ሆኖአል።

4 ሕያው አምላክን ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የጦር አዛዡን ቃል እግዚአብሔር አምላክህ ይሰማ ይሆናል፤ እግዚአብሔር አምላክህም ሰምቶ ይገሥጸው ይሆናል፤ ስለዚህ አንተም በሕይወት ለተረፉት ቅሬታዎች ጸልይ።”

5 የንጉሡ የሕዝቅያስ መልእክተኞች ወደ ኢሳይያስ መጡ፤

6 ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፤ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች እኔን ስለ ሰደቡኝ፣ በሰማኸው ቃል አትሸበር።

7 እነሆ፤ በላዩ መንፈስን እሰዳለሁ፤ ወሬም ሰምቶ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ በገዛ አገሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።’ ”