ኢሳይያስ 37:16-22 NASV

16 “በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር ባሉ መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርንም ፈጥረሃል።

17 አቤቱ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብል፤ አድምጥም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይኖችህን ክፈት፤ ተመልከትም። ሰናክሬም ሕያው አምላክን ለመሳደብ የላከውን ቃል ስማ።

18 “እግዚአብሔር ሆይ፤ በርግጥ የአሦር ነገሥታት እነዚህን ሕዝቦች፣ ምድራቸውንም ሁሉ ባድማ አድርገዋል።

19 አማልክታቸውን ወደ እሳት ጥለዋል፤ በሰው እጅ የተቀረጹ የድንጋይና የዕንጨት ምስሎች እንጂ አማልክት አልነበሩምና።

20 አሁንም፣ እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደሆንህ ያውቁ ዘንድ፣ አቤቱ ከእጁ አድነን።”

21 ከዚህ በኋላ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ሕዝቅያስ ላከ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ አሦር ንጉሥ፣ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ጸልየሃልና፣

22 እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤“ ‘ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ፣ንቃሃለች፣ አፊዛብሃለች፤የኢየሩሳሌም ልጅ፣አንተ ስትሸሽ ራሷን ነቅንቃብሃለች።