ኢሳይያስ 42:10-16 NASV

10 እናንት ወደ ባሕር የምትወርዱ፣ በዚያም ያላችሁ ሁሉ፣ደሴቶችና በዚያ የምትኖሩ በሙሉ፣ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፣ከምድር ዳርቻም ምስጋናውን ዘምሩ።

11 ምድረ በዳውና ከተሞቹ ድምፃቸውን ከፍ ያድርጉ፤ቄዳር ያለችበት መንደር ደስ ይበለው፤የሴላ ሕዝቦች በደስታ ይዘምሩ፤ከተራሮችም ራስ ላይ ይጩኹ።

12 ክብር ለእግዚአብሔር ይስጡ፤ምስጋናውንም በደሴቶች ያውጁ።

13 እግዚአብሔር እንደ ኀያል ሰው ይዘምታል፤እንደ ተዋጊ በወኔ ይነሣል፤የቀረርቶ ጩኸት ያሰማል፤ጠላቶቹንም ድል ያደርጋል።

14 “ለረጅም ጊዜ ዝም አልሁ፤ጸጥ አልሁ፤ ራሴንም ገታሁ፤አሁን ግን ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣እጮኻለሁ፤ ቁና ቁና እቃትታለሁ፤ እተነፍሳለሁ።

15 ተራራውንና ኰረብታውን አፈርሳለሁ፤ዕፀዋቱን ሁሉ አደርቃለሁ፤ወንዙንም ደሴት አደርጋለሁ፤ኵሬውን አደርቃለሁ።

16 ዕውሮችን በማያወቁት መንገድእመራቸዋለሁ፤ባልተለመደ ጐዳና እወስዳቸዋለሁ።ጨለማውን በፊታቸው ብርሃን አደርጋለሁ፤ጐርባጣውን ስፍራ አስተካክላለሁ።ይህን አደርጋለሁ፤አልተዋቸውም።