2 አይጮኽም፣ ቃሉን ከፍ አያደርግም፤ድምፁን በመንገድ ላይ በኀይል አያሰማም።
3 የተቀጠቀጠ ሸምበቆ አይሰብርም፤የሚጤስም የጧፍ ክር አያጠፋም፤ፍትሕን በታማኝነት ያመጣል።
4 ፍትሕን በምድር እስኪያመጣ ድረስ፣አይደክምም፤ ተስፋም አይቈርጥም፤ደሴቶች በሕጉ ይታመናሉ።”
5 ሰማያትን የፈጠረ፣ የዘረጋቸውም፣ምድርንና በውስጧ ያሉትን ሁሉ ያበጀ፣ለሕዝቧ እስትንፋስን፣ለሚኖሩባትም ሕይወትን የሚሰጥ፣ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
6 “እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤እጅህንም እይዛለሁ፤እጠብቅሃለሁ፤ለሕዝቡ ቃል ኪዳን፣ለአሕዛብም ብርሃን አደርግሃለሁ።
7 የዕውሮችን ዐይን ትከፍታለህ፤ምርኮኞችን ከእስር ቤት፣በጨለማ የተቀመጡትንም ከወህኒ ታወጣለህ።
8 “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው፤ክብሬን ለሌላ፣ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም።