1 “ለቀባሁት፣ ቀኝ እጁን ለያዝሁት፣ነገሥታትን ትጥቅ አስፈታ ዘንድ፣ሕዝብን ሁሉ ላስገዛለት፣ደጆች እንዳይዘጉ፣በሮቹን በፊቱ ለምከፍትለት፣ለቂሮስ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
2 ‘በፊትህ እሄዳለሁ፤ተራሮችን እደለድላለሁ፤የናስ በሮችን እሰብራለሁ፤የብረት መወርወሪያዎችንም እቈርጣለሁ።
3 በስምህ የምጠራህ የእስራኤል አምላክ፣እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቅ ዘንድ፣በተሰወረ ስፍራ የተከማቸውን ሀብት፣በጨለማም ያለውን ንብረት እሰጥሃለሁ።
4 ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፣ስለ መረጥሁት ስለ እስራኤል፣አንተ ባታውቀኝ እንኳ፣በስምህ ጠርቼሃለሁ፤የክብርም ስም ሰጥቼሃለሁ።