ኢሳይያስ 45:10-16 NASV

10 አባቱን፣‘የወለድኸው ምንድን ነው?’ ለሚል፣እናቱንም፣‘ምን ወለድሽ’? ለሚል ወዮለት።

11 “የእስራኤል ቅዱስ፣ ሠሪውም የሆነ እግዚአብሔር፣ስለሚመጡ ነገሮች እንዲህ ይላል፤‘ስለ ልጆቼ ትጠይቁኛላችሁን?ስለ እጆቼስ ሥራ ታዙኛላችሁን?

12 ምድርን የሠራሁ እኔ ነኝ፤ሰውንም በላይዋ ፈጥሬአለሁ፤እጆቼ ሰማያትን ዘርግተዋል፤የሰማይንም ሰራዊት አሰማርቻለሁ።

13 ቂሮስን በጽድቅ አስነሥቻለሁ፤መንገዱን ሁሉ አስተካክዬለታለሁ፤ከተማዬን እንደ ገና ይሠራታል፤ምርኮኞቼን ያለ ክፍያ ወይም ያለ ዋጋ፣ነጻ ያወጣል፤’ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”

14 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“የግብፅ ሀብትና የኢትዮጵያ ንግድ፣ቁመተ ረጃጅሞቹ የሳባ ሰዎች፣ወደ አንተ ይመጣሉ፤የአንተ ይሆናሉ፤ከኋላ ይከተሉሃል፤በሰንሰለትም ታስረው ወደ አንተ በመምጣት፣በፊትህ እየሰገዱ፣‘በእውነት እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ብለው ይለምኑሃል።”

15 አዳኙ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤አንተ በእውነት ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ።

16 ጣዖት ሠሪዎች ሁሉ ያፍራሉ፤ ይቀላሉ፤በአንድነት ይዋረዳሉ።