ኢሳይያስ 47:4-10 NASV

4 የሚቤዠን የእስራኤል ቅዱስ፣ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።

5 “አንቺ የባቢሎናውያን ልጅ ሆይ፤ወደ ጨለማ ግቢ፤ ዝም ብለሽም ተቀመጪ፤ከእንግዲህ የመንግሥታት እመቤት፣ተብለሽ አትጠሪም።

6 ሕዝቤን ተቈጥቼ ነበር፤ርስቴን አርክሼው ነበር፤አሳልፌ በእጅሽ ሰጠኋቸው፤አንቺ ግን አልራራሽላቸውም፤በዕድሜ በገፉት ላይ እንኳ፣እጅግ ከባድ ቀንበር ጫንሽባቸው።

7 አንቺም፣ ‘እስከ መጨረሻው፣ለዘላለም ንግሥት እሆናለሁ!’ አልሽ፤ሆኖም እነዚህን ነገሮች አላስተዋልሽም፤ፍጻሜያቸው ምን እንደሚሆንም አላሰብሽም።

8 “አሁንም አንቺ ቅምጥል ፍጡር፣በራስሽ ተማምነሽ የምትቀመጪ፣በልብሽም፣‘እኔ ነኝ፣ ከእኔ በቀር ሌላ የለም፤ከእንግዲህ መበለት አልሆንም፤የወላድ መካንም አልሆንም’ የምትይ ስሚ!

9 እነዚህ ሁለት ነገሮች፣መበለትነትና የወላድ መካንነት፣አንድ ቀን ድንገት ይመጡብሻል፤የቱን ያህል አስማት፣የቱንም ያህል መተት ቢኖርሽ፣በሙሉ ኀይላቸው ይመጡብሻል።

10 በክፋትሽ ተማምነሽ፣‘ማንም አያየኝም’ አልሽ፤ደግሞም፣ ‘እኔ ነኝ፣ ከእኔ በቀር ሌላ የለም’ባልሽ ጊዜ፣ጥበብሽና ዕውቀትሽ አሳሳቱሽ።