ኢሳይያስ 49:15-21 NASV

15 “እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለችን?ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን?ምናልባት እርሷ ትረሳ ይሆናል፣እኔ ግን እልረሳሽም።

16 እነሆ፤ በእጄ መዳፍ ላይ ቀርጬሻለሁ፤ቅጥሮችሽ ምንጊዜም በፊቴ ናቸው።

17 ወንዶች ልጆችሽ ፈጥነው ይመለሳሉ፤ያፈራረሱሽም ከአንቺ ይሸሻሉ።

18 ዐይንሽን ቀና አድርጊ፤ ዙሪያውንም ተመልከቺ፤ወንዶች ልጆችሽ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ።“በሕያውነቴ እምላለሁ፤እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፤እንደ ሙሽራም ትጐናጸፊያቸዋለሽ” ይላል እግዚአብሔር።

19 “ፈራርሰሽ ባድማ ብትሆኚ፣ምድርሽ ፈጽሞ ቢጠፋ፣ዛሬ ለሕዝብሽ ጠባብ ብትሆኚም እንኳ፣የዋጡሽ ከአንቺ ይርቃሉ።

20 በሐዘንሽ ዘመን የወለድሻቸው ልጆች፣ጆሮሽ እየሰማ፣‘ይህ ቦታ በጣም ጠቦናል፤የምንኖርበት በቂ ስፍራ ስጪን’ ይሉሻል።

21 በልብሽም እንዲህ ትያለሽ፣‘እነዚህን የወለደልኝ ማን ነው?እኔ ሐዘንተኛና መካን፣የተሰደድሁና የተጠላሁ ነበርሁ፤እነዚህን ማን አሳደጋቸው?ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ታዲያ፣ እነዚህ ከየት መጡ?’