ኢሳይያስ 51:1-6 NASV

1 “እናንት ጽድቅን የምትከታተሉ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልጉ ስሙኝ፤ተቈርጣችሁ የወጣችሁበትን ዐለት፣ተቈፍራችሁ የወጣችሁባትንም ጒድጓድ ተመልከቱ።

2 ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፣ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሣራ ተመልከቱ፤በጠራሁት ጊዜ አንድ ራሱን ብቻ ነበር፤ባረክሁት፤ አበዛሁትም።

3 እግዚአብሔር ጽዮንን በርግጥ ያጽናናታል፤ፍርስራሾቿንም በርኅራኄ ይመለከታል፤ምድረ በዳዋን እንደ ዔድን፣በረሓዋንም እንደ እግዚአብሔር ተክል ቦታ ያደርጋል፤ተድላና ደስታ፣ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ በእርሷ ይገኛሉ።

4 “ወገኔ ሆይ፤ አድምጠኝ፤ሕዝቤ ሆይ፤ ስማኝ፤ሕግ ከእኔ ይወጣል፤ፍርዴም ለሕዝቦች ብርሃን ይሆናል።

5 ጽድቄ በፍጥነት እየቀረበ፣ማዳኔም እየደረሰ ነው፤ክንዴም ለመንግሥታት ፍትሕን ያመጣል፤ደሴቶች ወደ እኔ ይመለከታሉ፤ክንዴንም በተስፋ ይጠብቃሉ።

6 ዐይኖቻችሁን ወደ ሰማያት አንሡ፤ወደ ታች ወደ ምድርም ተመልከቱ፤ሰማያት እንደ ጢስ በነው ይጠፋሉ፤ምድር እንደ ልብስ ታረጃለች፤ነዋሪዎቿም እንደ አሸን ፈጥነው ይረግፋሉ፤ማዳኔ ግን ለዘላለም ይኖራል፤ጽድቄም መጨረሻ የለውም።