ኢሳይያስ 52:1-7 NASV

1 ጽዮን ሆይ፤ ተነሺ፤ ተነሺ፤ኀይልን ልበሺ፤ቅድስቲቱ ከተማ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ!የክብር ልብስሽን ልበሺ፤ያልተገረዘ የረከሰምከእንግዲህ ወደ አንቺ አይገባም።

2 ትቢያሽን አራግፊ፤ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ተነሺ በዙፋንሽ ላይ ተቀመጪ፤ምርኮኛዪቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፤የዐንገትሽን የእስራት ሰንሰለት አውልቀሽ ጣዪ።

3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ያለ ዋጋ ተሸጣችሁ ነበር፤ያለ ገንዘብ ትቤዣላችሁ።”

4 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በመጀመሪያ ሕዝቤ ይኖር ዘንድ ወደ ግብፅ ወረደ፤በኋላም አሦር ያለ ምክንያት አስጨንቆ ገዛው።

5 “አሁን እዚህ ምን አለኝ?” ይላል እግዚአብሔር፤“ሕዝቤ ያለ ምክንያት ተወስዶአል፤የገዟቸው ተሣልቀውባቸዋል”ይላል እግዚአብሔር።“ቀኑን ሙሉ፣ስሜ ያለ ማቋረጥ ይሰደባል።

6 ስለዚህ ሕዝቤ ስሜን ያውቃል፤በዚያ ቀንም፣አስቀድሜ የተናገርሁ እኔ መሆኔን ይረዳል፤እነሆ፤ እኔው ነኝ።”

7 በተራሮች ላይ የቆሙ፣የምሥራች ይዘው የሚመጡ እግሮች፣ሰላምን የሚናገሩ፣መልካም ዜና የሚያበስሩ፣ድነትን የሚያውጁ፣ጽዮንንም፣“አምላክሽ ነግሦአል” የሚሉ እንዴት ያማሩ ናቸው።