1 የሰማነውን ነገር ማን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ?
2 በፊቱ እንደ ቡቃያ፣ከደረቅም መሬት እንደ ወጣ ሥር በቀለ፤የሚስብ ውበት ወይም ግርማ የለውም፤እንድንወደውም የሚያደርግ መልክ አልነበረውም።
3 በሰዎች የተናቀና የተጠላ፣የሕማም ሰውና ሥቃይ ያልተለየው ነበር።ሰዎች ፊታቸውን እንደሚያዞሩበት ዐይነት፣የተናቀ ነበር፤ እኛም አላከበርነውም።
4 በርግጥ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤ሕመማችንንም ተሸከመ፤እኛ ግን በእግዚአብሔር እንደ ተመታ፣እንደ ተቀሠፈ፣ እንደ ተሠቃየም ቈጠርነው።
5 ነገር ግን እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤ስለ በደላችንም ደቀቀ፤በእርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።