ኢሳይያስ 57:14-20 NASV

14 እንዲህ ይባላል፤“አብጁ፤ አብጁ፤ መንገድ አዘጋጁ፤ከሕዝቤ መንገድ ዕንቅፋት አስወግዱ።”

15 ከፍ ከፍ ያለውና ልዕልና ያለው እርሱ፣ስሙም ቅዱስ የሆነው፣ ለዘላለም የሚኖረው እንዲህ ይላል፤“የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት፣ከፍ ባለውና በቅዱሱ ስፍራ እኖራለሁ፤የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋር እሆናለሁ።

16 የሰው መንፈስ በፊቴ እንዳይዝል፣የፈጠርሁትም ሰው እስትንፋስ እንዳይቆም፣ለዘላለም አልወቅስም፤ሁልጊዜም አልቈጣም።

17 ኀጢአት ስለ ሞላበት ስግብግብነቱ ተቈጣሁት፤ቀጣሁት፤ ፊቴንም በቍጣ ከእርሱ ሸሸግሁ፤ያም ሆኖ በገዛ መንገዱ ገፋበት።

18 መንገዶቹን አይቻለሁ፤ ቢሆንም እፈውሰዋለሁ፤እመራዋለሁ፤ ለእርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱትምመጽናናትን እመልሳለሁ፤

19 በእስራኤል አልቃሾች ከንፈር ላይ ምስጋና እፈጥራለሁ።በቅርብና በሩቅ ላሉት ሰላም፣ ሰላም ይሁን፤እኔ እፈውሳቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።

20 ክፉዎች ግን ማዕበሉ ጭቃና ጒድፍ እንደሚያወጣ፣ጸጥ ማለት እንደማይችል፣እንደሚናወጥ ባሕር ናቸው።