1 ንጉሥ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን ከፍ ባለና በከበረ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፤ የልብሱም ዘርፍ ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር።
2 ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፤ እያንዳንዳቸውም ስድስት ክንፍ ነበራቸው። በሁለት ክንፍ ፊታቸውን ይሸፍኑ ነበር፤ በሁለት ክንፍ እግራቸውን ይሸፍኑ ነበር፤ በሁለቱም ክንፍ ይበሩ ነበር፤
3 እርስ በርሳቸው በመቀባበልም“ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ምድር ሁሉ በክብሩ ተሞልታለችቃ ይሉ ነበር።
4 ከድምፃቸው ጩኸት የተነሣ የመድረኩ መሠረት ተናወጠ፤ ቤተ መቅደሱም በጢስ ተሞላ።
5 እኔም፣ “ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው ነኝ፤ የምኖረውም ከንፈሮቹ በረከሱበት ሕዝብ መካከል ነው፤ ዐይኖቼም ንጉሡን፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አይተዋልና ጠፍቻለሁ፣ ወዮልኝ!” አልሁ።
6 ከዚያም ከሱራፌል አንዱ፣ ከመሠዊያው ላይ የእሳት ፍም በጒጠት ወስዶ፣ ወደ እኔ እየበረረ መጣ።