ዘሌዋውያን 16:17-23 NASV

17 አሮን ለማስተሰረይ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለራሱ፣ ለቤተሰቡና ለእስራኤል ማኅበረሰብ ሁሉ አስተሰርዮ እስኪወጣ ድረስ ማንም ሰው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አይገኝ።

18 “ከዚያም መጥቶ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወዳለው መሠዊያ ይምጣ፤ ለመሠዊያውም ያስተሰርይለት፤ ከወይፈኑና ከፍየሉ ደም ወስዶ የመሠዊያውን ቀንዶች ሁሉ ያስነካ፤

19 ከእስራኤላውያንም ርኵሰት መሠዊያውን ለማንጻትና ለመቀደስ ከደሙ ወስዶ በጣቱ ሰባት ጊዜ ይርጭበት።

20 “አሮን ለቅድስተ ቅዱሳኑ፣ ለመገናኛው ድንኳንና ለመሠዊያው የሚያደርገውን ስርየት ከፈጸመ በኋላ በሕይወት ያለውን ፍየል ወደ ፊት ያቅርበው፤

21 ሁለት እጆቹን በሕይወት ባለው ፍየል ራስ ላይ ይጫን፤ በላዩም የእስራኤላውያንን ክፋትና ዐመፅ፣ ኀጢአታቸውን ሁሉ በሙሉ ይናዘዝበት፤ እነዚህንም በፍየሉ ራስ ላይ ይጫን፤ ፍየሉንም ለዚሁ ተግባር በተመደበ ሰው እጅ ወደ ምድረ በዳ ይስደደው።

22 ፍየሉም ኀጢአታቸውን ሁሉ ተሸክሞ ወደ ምድረ በዳ ይሄዳል፤ ሰውየውም ፍየሉን ሰው ሊኖርበት በማይችል ስፍራ ይልቀቀው።

23 “ከዚህ በኋላ አሮን ወደ መገናኛው ድንኳን ሄዶ፣ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ሊገባ ሲል የለበሳቸውን የበፍታ ልብሶች አውልቆ፣ በዚያው ይተዋቸው።