7 የእህል ቊርባንህ በመጥበሻ የሚበስል ከሆነ፣ ከላመ ዱቄትና ከዘይት ይዘጋጅ።
8 በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀውን የእህል ቊርባን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) አምጥተህ ለካህኑ አስረክብ፤ ካህኑም ወደ መሠዊያው ይወስደዋል፤
9 ከእህሉም ቊርባን ላይ ለመታሰቢያ የሚሆነውን ክፍል ያነሣና በእሳት የሚቃጠል፣ ሽታውም እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል።
10 የተረፈውም ቊርባን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ፤ ይህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርበው ቊርባን እጅግ የተቀደሰ ክፍል ነው።
11 “ ‘ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት በምታቀርቡት ቊርባን ውስጥ እርሾ ወይም ማር ጨምራችሁ ማቃጠል ስለማይገባችሁ፣ በምታቀርቡት በማንኛውም የእህል ቊርባን እርሾ አይኑርበት።
12 እነዚህን የበኵራት ቊርባን አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ማቅረብ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ሽታው ደስ የሚያሰኝ ቊርባን ሆነው በመሠዊያ ላይ ለመቃጠል አይቀርቡም።
13 የምታቀርበውን የእህል ቊርባን ሁሉ በጨው ቀምመው፤ የአምላክህ (ኤሎሂም) የቃል ኪዳን ጨው ከእህል ቊርባንህ አይታጣ፤ በቊርባንህም ላይ ጨው ጨምርበት።