ዘኁልቍ 6:12-18 NASV

12 ራሱን የተለየ ያደረገበትን ጊዜ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መቀደስ አለበት፤ እንዲሁም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት የበደል መሥዋዕት አድርጎ ያምጣ። ያለፉት ቀኖች አይቈጠሩም፤ በተለየበት ጊዜ ረክሶአልና።

13 “ ‘እንግዲህ ናዝራዊ የመለየቱ ጊዜ ሲያበቃ ሥርዐቱ ይህ ነው፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ እንዲመጣ ይደረጋል።

14 እዚያም መሥዋዕቱን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቅርብ፤ ይኸውም፣ እንከን የሌለበት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ እንከን የሌለበት የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኀጢአት መሥዋዕት እንዲሁም እንከን የሌለበት አውራ በግ ለኅብረት መሥዋዕት ሲሆን፣

15 ከእነዚህም ጋር የሚቀርበውን የእህልና የመጠጥ ቍርባን ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ማለት ከላመ ዱቄት በዘይት የተለወሱ ዕንጎቻዎች እንዲሁም በስሱ የተጋገረና ዘይት የተቀባ ስስ ቂጣ ያምጣ።

16 “ ‘ካህኑ እነዚህን የኀጢአት መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቀርባል።

17 በመሶብ ያለውን እርሾ የሌለበት ቂጣ እንዲሁም አውራ በጉን የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ከእህሉና ከመጠጡ ቍርባን ጋር ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቅርብ።

18 “ ‘ከዚያም ናዝራዊው ተስሎ የተለየበትን ጠጒር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይላጨው፤ ጠጒሩንም ወስዶ ከኅብረቱ መሥዋዕት ሥር በሚነደው እሳት ውስጥ ይጨምረው።