ዘኁልቍ 9:15-21 NASV

15 ማደሪያው በተተከለ ዕለት ደመናው የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከምሽት እስከ ንጋት ድረስ ማደሪያውን የሸፈነው ደመና እሳት ይመስል ነበር።

16 ይህ በዚህ ሁኔታ ቀጠለ፤ ደመናው ማደሪያውን ሸፈነው፤ በሌሊትም የእሳት መልክ ነበረው።

17 ደመናው ከድንኳኑ ላይ በሚነሣበት ጊዜ እስራኤላውያን ጒዞአቸውን ይጀምሩ ነበር፤ ደመናው በሚቆምበት ቦታ ደግሞ ይሰፍሩ ነበር፤

18 እስራኤላውያን ጒዞ የሚጀምሩትም ሆነ የሚሰፍሩት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ነበር። ደመናው በድንኳኑ ላይ በሚቈይበት ጊዜ ሁሉ ከሰፈር አይንቀሳቀሱም ነበር።

19 ደመናው በድንኳኑ ላይ ብዙ ቀን ቢቈይም እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ትእዛዝ ይጠብቃሉ እንጂ ተነሥተው አይጓዙም።

20 አንዳንድ ጊዜ ደመናው በድንኳኑ ላይ የሚቈየው ለጥቂት ቀን ብቻ ነበር፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ይሰፍራሉ፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ትእዛዝ ጒዞ ይጀምራሉ፤

21 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ደመናው ከምሽት እስከ ንጋት ብቻ ይቈያል፤ ደመናው ንጋት ላይ ሲነሣም ጒዞአቸውን ይጀምራሉ፤ ቀንም ይሁን ሌሊት ደመናው ከተነሣ ጒዞ ይጀምራሉ።