22 በእነዚህ አስጸያፊ ተግባሮችሽና አመንዝራነትሽ ሁሉ፣ ከእናትሽ ማሕፀን እንደ ወጣሽ ዕርቃንሽን ሆነሽ በደምሽ ውስጥ ስትንፈራገጪ የነበርሽበት የሕፃንነትሽ ወራት ትዝም አላለሽ!።
23 “ ‘ወዮ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከሌላው ክፋትሽ ሁሉ በተጨማሪ፣
24 ለራስሽ ጒብታን አበጀሽ፤ በየአደባባዩም የማምለኪያ ኰረብታ ሠራሽ።
25 በየመንገዱ መጠምዘዣ ላይም የመስገጃ ኰረብታ አበጀሽ፤ ገላሽን ለዐላፊ አግዳሚው በማቅረብና አመንዝራነትሽን በማበራከት ውበትሽንም አረከስሽ።
26 ዘማውያን ከሆኑ ግብፃውያን ጎረቤቶችሽ ጋር አመነዘርሽ፤ ገደብ በሌለው የዝሙት ተግባርሽም ለቍጣ አነሣሣሽኝ።
27 ስለዚህ ክንዴን በአንቺ ላይ አንሥቼ ድርጎሽን ቀነስሁ፤ ከክፉ መንገድሽም የተነሣ በብልግናሽ ለሚያፍሩ ጠላቶችሽ ለፍልስጥኤማውያን ሴቶች ልጆች አሳልፌ ሰጠሁሽ።
28 ገና ስላልረካሽም ከአሦራውያን ጋር ደግሞ አመነዘርሽ፤ ከዚያም በኋላ እንኳ አልረካሽም።