ሕዝቅኤል

ምዕራፎች 24

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

የድስቱ ምሳሌ

1በዘጠነኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በዐሥረኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን ቀን፣ የዛሬውን ዕለት ለይተህ መዝግብ፤ የባቢሎን ንጉሥ ኢየሩሳሌምን በዚህ ቀን ከቦአታልና። 3ለዚህ ዐመፀኛ ቤት እንዲህ ብለህ ተምሳሌት ተናገር፤ ‘ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ብረት ድስት በእሳት ላይ ጣድ፤ከጣድህም በኋላ ውሃ ጨምርበት። 4ሙዳ፣ ሙዳ ሥጋ፣ምርጥ ምርጡን ቍርጥ ሁሉ፣ ጭንና ወርቹን ጨምርበት፤የተመረጡ ዐጥንቶችንም ሙላበት። 5ከመንጋው ሙክቱን ውሰድ፤ዐጥንቱን ለማብሰል ብዙ ማገዶ ከሥሩ ጨምር፤ሙክክ እስከሚል ቀቅለው፤ዐጥንቱም ይብሰል። 6“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤“ ‘ለዛገችው ብረት ድስትዝገቷም ለማይለቅ፣ደም ላፈሰሰችው ከተማ ወዮላት!መለያ ዕጣ ሳትጥልአንድ በአንድ አውጥተህ ባዶ አድርገው። 7“ ‘የሰው ደም በመካከሏ አለ፤በገላጣ ዐለት ላይ አደረገችው እንጂ፣ዐፈር ሊሸፍነው በሚችል፣በመሬት ላይ አላፈሰሰችውም። 8ቍጣዬ እንዲነድና ለመበቀል እንዲያመቸኝ፣ይሸፈንም ዘንድ እንዳይችል፣ደሟን በገላጣ ዐለት ላይ አፈሰስሁ። 9“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ደም ላፈሰሰችው ከተማ ወዮላት!እኔም ደግሞ የምትቃጠልበትን ማገዶ እቈልላለሁ። 10ማገዶውን ከምርበት፤እሳቱን አንድድ፤ቅመም ጨምረህበት፣ሥጋውን በሚገባ ቀቅል፤ዐጥንቱም ይረር። 11ጒድፉ እንዲቀልጥ፣ዝገቱም በእሳት እንዲበላ፣ባዶው ድስት እስኪሞቅ፣መደቡም እስኪግል ከሰል ላይ ጣደው። 12ብዙ ጒልበት ቢፈስበትም፣የዝገቱ ክምር፣በእሳት እንኳ፣ ሊለቅ አልቻለም። 13“ ‘የረከስሽው በብልግናሽ ነው፤ ቍጣዬ በአንቺ ላይ እስኪፈጸም ድረስ ከእንግዲህ ንጹሕ አትሆኚም፤ ከርኵሰትሽ ላነጻሽ ፈልጌ፣ መንጻት አልወደድሽምና። 14“ ‘እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ የምሠራበትም ጊዜ ደርሶአል፤ ወደ ኋላ አልልም፤ አልራራም፤ አላመነታምም። እንደ መንገድሽና እንደ ተግባርሽ ይፈረድብሻል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

የሕዝቅኤል ሚስት መሞት

15 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 16“የሰው ልጅ ሆይ፤ የዐይንህ ማረፊያ የሆነውን ነገር በመቅሠፍት እወስድብሃለሁ፤ አንተ ግን ዋይታ አታሰማ፤ አታልቅስ፤ እንባህንም አታፍስስ፤ 17ድምፅህን ዝቅ አድርገህ በሐዘን አንጐራጒር እንጂ ለሞተው አታልቅስ። ጥምጥምህን ከራስህ አታውርድ፤ ጫማህንም አታውልቅ፤ አፍህ ድረስ አትሸፋፈን፤ የዕዝን እንጀራም አትብላ።” 18እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፤ ሚስቴም ማታውኑ ሞተች፤ በማግሥቱም ጠዋት እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ። 19ሕዝቡም፣ “ይህን ስታደርግ ለእኛ የምታስተላልፈው መልእክት ምን እንደሆነ አትነግረንምን?” አሉኝ። 20እኔም እንዲህ አልኋቸው፤ “የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 21ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የኀይላችሁን ትምክሕት፣ የዐይናችሁ ማረፊያና የልባችሁ ደስታ የሆነውን መቅደሴን አረክሳለሁ። ትታችኋቸው የሄዳችሁ ወንድና ሴት ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 22እኔ እንዳደረግሁም ታደርጋላችሁ፤ አፋችሁ ድረስ አትሸፋፈኑም፤ የዕዝን እንጀራም አትበሉም፤ 23ጥምጥማችሁን ከራሳችሁ አታወርዱም፤ ጫማችሁንም አታወልቁም። በኀጢአታችሁ ትመነምናላችሁ፤ እርስ በርስ ታቃስታላችሁ እንጂ ሐዘን አትቀመጡም፤ አታለቅሱምም። 24ሕዝቅኤል ምልክት ይሆናችኋል፤ እርሱ እንዳደረገው ታደርጋላችሁ፤ ይህ በሚሆንበት ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ” 25“አንተም የሰው ልጅ ሆይ፤ ኀይላቸውን፣ ደስታቸውንና፣ ክብራቸውን፣ የዐይናቸው ማረፊያና የልባቸው ደስታ የሆኑትን ወንድና ሴት ልጆቻቸውን ጭምር በምወስድባቸው ቀን፣ 26በዚያን ቀን፣ ያመለጠ ሰው ይህን ወሬ ሊነግርህ ወደ አንተ ይመጣል፤ 27በዚያን ቀን አፍህ ተከፍቶ ከእርሱ ጋር ትነጋገራለህ፤ ከዚያም በኋላ እንደ ድዳ አትሆንም፤ ምልክትም ትሆናቸዋለህ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።”