ሕዝቅኤል 25 NASV

በአሞን ላይ የተነገረ ትንቢት

1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ አሞናውያን አድርገህ፣ ትንቢት ተናገርባቸው፤

3 እንዲህም በላቸው፤ ‘የጌታ፣ እግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “መቅደሴ በረከሰ ጊዜ፣ የእስራኤልም ምድር ባድማ በሆነች ጊዜ፣ የይሁዳም ቤት ተማርኮ በተወሰደ ጊዜ፣ ‘እሰይ’ ብላችኋልና፣

4 ለምሥራቅ ሕዝብ ትገዙ ዘንድ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ እነርሱም በመካከላችሁ ይሰፍራሉ፤ ድንኳኖቻቸውንም በዚያ ይተክላሉ፤ ፍሬያችሁን ይበላሉ፤ ወተታችሁንም ይጠጣሉ።

5 የራባን ከተማ የግመሎች መሰማሪያ፣ አሞንንም የበጎች መመሰጊያ አደርጋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።”

6 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “በልባችሁ ክፋት ሁሉ፣ በእስራኤል ውድቀት ላይ በመደሰት በእጃችሁ አጨብጭባችኋልና፤ በመዝለልም ጨፍራችኋልና

7 ክንዴን በእናንተ ላይ አነሣለሁ፤ በአሕዛብ እንድትበዘበዙ አደርጋለሁ፤ ከሕዝቦች መካከል አውጥቼ፣ ከአገሮችም ለይቼ አጠፋችኋለሁ፤ እደመስሳችኋለሁም። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”

በሞዓብ ላይ የተነገረ ትንቢት

8 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሞዓብና ሴይር፣ “እነሆ የይሁዳ ቤት እንደ ሌሎቹ አሕዛብ ሁሉ ሆነ” ብለዋልና፤

9 በምድሪቱ ድንበር ላይ ካሉትና ክብሯ ከሆኑት ከተሞች ከቤት የሺሞት፣ ከበአልሜዎንና ከቂርያታይም ጀምሬ የሞዓብን ዐምባ እገልጣለሁ።

10 ሞዓባውያንንም ከአሞናውያን ጋር ይገዙላቸው ዘንድ ለምሥራቅ ሕዝብ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ አሞናውያን በአሕዛብ ዘንድ ከእንግዲህ መታሰቢያ አይኖራቸውም።

11 ሞዓብንም እቀጣለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት

12 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ኤዶም የይሁዳን ቤት ተበቅሎአልና፤ በዚህም በደለኛ ሆኖአልና፤

13 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ክንዴን በኤዶም ላይ አነሣለሁ፤ ሰዎቹንና እንስሶቻቸውን እገድላለሁ፤ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ከቴማንም ጀምሮ እስከ ድዳን ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ።

14 በሕዝቤ በእስራኤል አማካይነት ኤዶምን እበቀላለሁ፤ እነርሱም እንደ ቍጣዬና እንደ መዓቴ መጠን በኤዶም ሕዝብ ላይ ያደርጋሉ፤ ኤዶማውያንም በቀሌን ያውቃሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ትንቢት

15 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ፍልስጥኤማውያን በቂም ተነሣሥተው በክፉ ልብ ተበቅለዋልና፣ ይሁዳንም በቈየ ጠላትነት ለማጥፋት ፈልገዋልና፤

16 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ክንዴን በፍልስጥኤማውያን ላይ አነሣለሁ፤ ከሊታውያንንም እቈርጣለሁ፤ በባሕሩ ጠረፍ ላይ የቀሩትንም አጠፋለሁ።

17 በታላቅ በቀል እበቀላቸዋለሁ፤ በመዓቴም እቀጣቸዋለሁ፤” በምበቀላቸውም ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48