1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ራሳቸውን ብቻ ለሚንከባከቡ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች መንጋውን ማሰማራት አልነበረባቸውምን?
3 ጮማውን ትበላላችሁ፤ ከጠጒሩ የተሠራውን ሱፍ ትለብሳላችሁ፤ የሰባውን ዐረዳችሁ፤ ነገር ግን መንጋውን አትንከባ ከቡትም።
4 ደካማውን አላበረታችሁትም፤ በሽተኛውን አልፈወሳችሁትም፤ የተጐዳውንም አልጠገናችሁትም። የባዘኑትን አልመለሳችሁም፤ የጠፉትንም አልፈለጋችሁም፤ በግፍና በጭካኔ ገዛችኋቸው።
5 ስለዚህ እረኛ የለምና ተበተኑ፤ በመበተናቸውም ለአራዊቱ ሁሉ መብል ሆኑ።
6 በጎቼ በየተራራው ሁሉና በየኰረብታው ላይ ተንከራተቱ። በምድር ሁሉ ተበተኑ፤ የፈለጋቸውም፤ የፈቀዳቸውም የለም።
7 “ ‘ስለዚህ እናንት እረኞች፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤
8 በሕያውነቴ እምላለሁ፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እረኞቼ መንጋዬን ስላልፈለጉ፣ ከመንጋዬም ይልቅ ራሳቸውን ስለተንከባከቡ፣ መንጋዬ እረኛ አጥቶ ለንጥቂያ ተዳርጎአል፤ ለአራዊትም ሁሉ መብል ሆኖአል።
9 ስለዚህ እረኞች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤
10 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ በእረኞች ላይ ተነሥቻለሁ፤ ስለ መንጋዬ እጠይቃቸዋለሁ፤ ከእንግዲህ እረኞች ራሳቸውን መመገብ እንዳይችሉ፣ መንጋዬን እንዳያሰማሩ አደርጋለሁ። መንጋዬን ከአፋቸው አስጥላለሁ፤ ከእንግዲህም ምግብ አይሆናቸውም።
11 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋቸዋለሁ፤ እጠብቃቸዋለሁም።
12 እረኛ ከመንጋው ጋር ሳለ፣ የተበተኑበትን በጎች እንደሚፈልግ ሁሉ፣ እኔም በጎቼን እፈልጋለሁ። በደመናና በጨለማቀን ከተበተኑበት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ።
13 ከአሕዛብ መካከል አወጣቸዋለሁ፤ ከየአገሮቹ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ። በእስራኤል ተራሮች፣ በየወንዙ ዳርና፣ በምድሪቱ መኖሪያዎች ሁሉ እንዲሰማሩ አደርጋለሁ።
14 በመልካሙ ስፍራ አሰማራቸዋለሁ፤ የእስራኤል ተራሮች ከፍታም የግጦሽ መሬት ይሆናቸዋል። በመልካሙ ግጦሽ መሬት ላይ ይተኛሉ፤ እዚያም በእስራኤል ተራሮች ለምለም መስክ ላይ ይመገባሉ።
15 እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ፤ አስመስጋቸዋለሁም። ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
16 የጠፉትን እፈልጋለሁ፤ የባዘኑትንም እመልሳለሁ። የተጐዱትን እጠግናለሁ፤ የደከሙትንም አበረታለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውን ግን አጠፋለሁ። መንጋውን በፍትሕ እጠብቃለሁ።
17 “ ‘መንጋዬ ስለ ሆናችሁት ስለ እናንተ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በበግና በበግ መካከል፣ በአውራ በግና በአውራ ፍየል መካከል እፈርዳለሁ።
18 በለምለሙ መስክ ላይ መመገቡ አይበቃችሁምን? የተረፈውን መሰማሪያችሁን ደግሞ በእግራችሁ መረጋገጥ ይገባችኋልን? ንጹሕ ውሃ መጠጣቱ አይበቃችሁምን? የተረፈውንስ በእግራችሁ ማደፍረስ ይገባችኋልን?
19 መንጋዬ የረጋገጣችሁትን መመገብና በእግራችሁ ያደፈረሳችሁትን መጠጣት ይገባዋልን?
20 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፤ “እነሆ እኔ ራሴ በሰባው በግና በከሳው በግ መካከል እፈርዳለሁ።
21 ደካሞቹን በጎች በጐናችሁና በትከሻችሁ ስለምት ገፈትሩ፣ እስኪባረሩም ድረስ በቀንዳችሁ ስለምትወጓቸው፣
22 እኔ መንጋዬን አድናለሁ፤ ከእንግዲህ ለንጥቂያ አይዳረጉም፤ በአንዱ በግና በሌላውም በግ መካከል እፈርዳለሁ።
23 በእነርሱ ላይ አንድ እረኛ፣ ባሪያዬን ዳዊትን አቆማለሁ፤ እርሱም ያሰማራቸዋል፤ እረኛቸውም ይሆናል።
24 እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እሆናለሁ፤ ባሪያዬ ዳዊትም በመካከላቸው ገዥ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።”
25 “ ‘ከእነርሱ ጋር የሰላም ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚያም ምድሪቱን ከዱር አራዊት ነጻ አደርጋለሁ፤ እነርሱም በምድረ በዳ ይኖራሉ፤ በደንም ውስጥ በሰላም ይተኛሉ።
26 እነርሱንና በኰረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች እባርካለሁ። በወቅቱም ዝናብ አወርድላቸዋለሁ፤ ዝናቡም የበረከት ዝናብ ይሆናል።
27 የየሜዳው ዛፍ ፍሬ ይሰጣል፤ መሬቱም እህል ያበቅላል። ሕዝቡም በምድሪቱ ላይ በሰላም ይኖራሉ። የቀንበሮቻቸውን ማነቆ ሰብሬ በባርነት ከገዟቸው እጅ ሳድናቸው፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።
28 ከእንግዲህ ለሌሎች ሕዝቦች ንጥቂያ አይዳረጉም፤ የዱር አራዊት አይቦጫጭቋቸውም፤ በሰላም ይኖራሉ፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።
29 ከእንግዲህ በምድሪቱ ላይ የራብ ተጠቂ እንዳይሆኑ፣ የአሕዛብንም ስድብ እንዳይሸከሙ ፍሬ በመስጠት የታወቀውን መሬት እሰጣቸዋለሁ።
30 ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ከእነርሱ ጋር እንደሆንሁ፤ የእስራኤል ቤት የሆኑት እነርሱም ሕዝቤ እንደሆኑ ያውቃሉ፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
31 እናንተ በጎቼ የማሰማሪያዬ በጎች ያልኋችሁ፣ ሕዝብ ናችሁ፤ እኔም አምላካችሁ ነኝ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።