1 በስድስተኛው ዓመት፣ በስድስተኛው ወር፣ በአምስተኛው ቀን በቤቴ ተቀምጬ ሳለሁ፣ የይሁዳም ሽማግሌዎች በፊቴ ተቀምጠው ሳሉ፣ በዚያ የጌታ እግዚአብሔር እጅ በላዬ መጣች።
2 እኔም አየሁ፤ እነሆ፤ የሰውን ልጅ የሚመስል ነበረ፤ ወገቡ ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ታች እንደ እሳት ያለ ነበር፤ ወገቡንም ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ላይ እንደ ጋለ ብረት ያበራ ነበር።
3 እርሱም እጅ መሳይ ዘርግቶ የራስ ጠጒሬን ያዘ፤ መንፈስም በምድርና በሰማይ መካከል አነሣኝ፤ እርሱም ቅናት የሚያነሣው ጣዖት ወደ ቆመበት፣ ወደ ውስጠኛው አደባባይ መግቢያ ወደ ሰሜን በር ወደ ኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ራእይ ወሰደኝ።
4 እነሆ፤ በረባዳው ስፍራ በራእይ ያየሁት የእስራኤል አምላክ ክብር በዚያ ነበረ።
5 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ወደ ሰሜን ተመልከት” አለኝ። እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ ከመሠዊያው በር በሰሜን በኩል መግቢያው ላይ ይህ የቅናት ጣዖት ነበረ።
6 ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት ከመቅደሴ ያርቀኝ ዘንድ በዚህ የሚያደርገውን እጅግ አስጸያፊ ነገር ታያለህን? ከዚህም የባሰ አስጸያፊ ነገር ታያለህ” አለኝ።
7 ከዚያም በኋላ ወደ አደባባዩ መግቢያ አመጣኝ፤ እኔም ግንቡን ተመለከትሁ፤ ቀዳዳም ነበረበት።
8 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ግንቡን ንደለው” አለኝ፤ እኔም ግንቡን ነደልሁት፤ አንድ በርም አገኘሁ።
9 እርሱም፣ “ግባና በዚህ የሚፈጽሙትን እጅግ የከፋ ርኵሰት ተመልከት አለኝ።
10 እኔም ገብቼ አየሁ፤ እነሆ በደረታቸው የሚሳቡ ፍጡራንና የርኵሳን አራዊት ዐይነት ሁሉ፣ የእስራኤልም ቤት ጣዖታት ሁሉ ዙሪያውን በግንቡ ላይ ተቀርጸው ነበር።
11 በእነዚህም ፊት ከእስራኤል ቤት ሰባ ሽማግሌዎች ቆመው ነበር፤ በመካከላቸውም የሳፋን ልጅ ያእዛንያ ቆሞ ነበር፤ እያንዳንዳቸውም በእጃቸው ጥና ይዘዋል፤ መልካም መዐዛ ያለው የዕጣን ጢስም እየተትጐለጐለ ይወጣ ነበር።
12 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች እያንዳንዳቸው በጣዖታቸው ምስል ጓዳ ውስጥ በጨለማ የሚያደርጉትን አይተሃልን? እነርሱ፣ ‘እግዚአብሔር አያየንም፤ እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአል” ይላሉ” አለኝ።
13 ደግሞም፣ “ከእነዚህ የባሰ አስጸያፊ ነገር ሲሠሩ ታያለህ” አለኝ።
14 ከዚህም በኋላ በሰሜን በኩል ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በር መግቢያ አመጣኝ፤ በዚያም ሴቶች ተቀምጠው ተሙዝ ለተባለው ጣዖት ሲያለቅሱ አየሁ።
15 እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን አይተሃልን? ከዚህም የባሰ አስጸያፊ ነገር ታያለህ” አለኝ።
16 ደግሞም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ እነሆም በመተላለፊያውና በመሠዊያው መካከል በቤተ መቅደሱ መግቢያ ላይ ሃያ አምስት ሰዎች ያህል ነበሩ፤ ጀርባቸውን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አድርገው ለምትወጣዋ ፀሓይ ይሰግዱ ነበር።
17 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን አይተሃልን? የይሁዳ ቤት በዚህ ቦታ የሚፈጽሙት ጸያፍ ተግባር ቀላል ነገር ነውን? ምድሪቱንስ በዐመፅ በመሙላት ዘወትር ያስቈጡኝ ዘንድ ይገባልን? እነሆ፤ ቅርንጫፉን ወደ አፍንጫቸው አቅርበዋል!
18 ስለዚህ በቍጣ እመጣባቸዋለሁ፤ በርኅራኄ ዐይን አላያቸውም፤ ከሚመጣባቸው ነገር አላድናቸውም፤ ወደ ጆሮዬም ቢጮኹ አልሰማቸውም።”