ሕዝቅኤል 18 NASV

ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ ትሞታለች

1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2 “ስለ እስራኤል ምድር፣“ ‘አባቶች ጐምዛዛ የወይን ፍሬ በሉ፤የልጆችንም ጥርስ አጠረሰ’ እያላችሁ የምትመስሉት ተምሳሌት ምን ለማለት ነው?

3 “በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ልዑል እግዚአብሔር፤ ከእንግዲህ ይህን ምሳሌ በእስራኤል ምድር አትመስሉም።

4 እነሆ ነፍስ ሁሉ የእኔ ናት፤ የአባት ነፍስ የእኔ እንደሆነች ሁሉ የልጁም ነፍስ የእኔ ናት፤ ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።

5 “በቅንነትና በትክክል የሚሠራ፣ጻድቅ ሰው ቢገኝ፣

6 በኰረብታ ባሉ አብያተ ጣዖት የቀረበውን አይበላም፤በእስራኤል ቤት ወዳሉት ጣዖታት አይመለከትምየባልንጀራውን ሚስት አያባልግም፤ከሴት ጋር በወር አበባዋ ጊዜ አይተኛም።

7 ማንንም አይጨቍንም፤ነገር ግን በመያዣ የወሰደውን እንኳ ለተበዳሪው ይመልሳል፤ለተራበ የራሱን እንጀራ፣ለተራቈተም ልብስ ይሰጣል እንጂ፣በጒልበት አይቀማም።

8 በዐራጣ አያበድርም፣ከፍተኛ ወለድም አይቀበልም።እጁን ከበደል ይሰበስባል፤በሰውና በሰው መካከል በትክክል ይፈርዳል።

9 ሥርዐቴን ይከተላል፤ሕጌንም በቅንነት ይጠብቃል።ይህ ሰው ጻድቅ ነው፤ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል፤ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

10 “ነገር ግን ይህ ሰው ደም የሚያፈስ ወይም ከሚከተሉት ኀጢአቶች ማንኛውንም የሚፈጽም ዐመፀኛ ልጅ ቢኖረው፣

11 አባትየው አንዱንም ባያደርግ፣“ልጁ ግን በኰረብታ መስገጃ የቀረበውን ቢበላ፣የባልንጀራውን ሚስት ቢያባልግ፣

12 ድኻውንና ችግረኛውን ቢጨቍን፣በጒልበት ቢቀማ፣በመያዣነት የወሰደውን ባይመልስ፣ወደ ጣዖታት ቢመለከት፣አስጸያፊ ተግባራትን ቢፈጽም፣

13 በዐራጣ ቢያበድር፤ ከፍተኛ ወለድም ቢቀበል፣እንዲህ ዐይነቱ ሰው በሕይወት ይኖራልን? ከቶ አይኖርም! እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች አድርጓልና በእርግጥ ይሞታል፤ ደሙም በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል።

14 “ይህም ልጅ ደግሞ በተራው ልጅ ቢወልድና ልጁም አባቱ ያደረገውን ኀጢአት ሁሉ አይቶ ባይፈጽም፣ ይኸውም፦

15 በኰረብታ መስገጃ የቀረበውን ባይበላ፣በእስራኤል ቤት ወዳሉት ጣዖታት ባይመለከት፣የባልንጀራውን ሚስት ባያባልግ፣

16 ሰውን ባይጨቍን፣ብድር ለመስጠት መያዣ ባይጠይቅ፣በጒልበቱ ባይቀማ፣ነገር ግን ምግቡን ለተራበ፣ልብሱን ለተራቈተ ቢሰጥ፣

17 እጁን ደኻን ከመበደል ቢሰበስብ፣ዐራጣ ወይም ከፍተኛ ወለድ ባይቀበል፣ሕጌን ቢጠብቅ፣ ሥርዐቴንም ቢከተል፣በሕይወት ይኖራል እንጂ በአባቱ ኀጢአት አይሞትም።

18 አባቱ ግን የሰውን መብት ስለደፈረ፣ ወንድሙን በጒልበት ስለ ቀማና በሕዝቡ መካከል የማይገባውን ስላደረገ በገዛ ኀጢአቱ ይሞታል።

19 “እናንተ ግን፣ ‘ልጅ ስለ አባቱ ኀጢአት ለምን አይቀጣም?’ ትላላችሁ። ልጁ ቀናና ትክክለኛውን ነገር ስላደረገ፣ ሥርዐቴንም ሁሉ በጥንቃቄ ስለ ጠበቀ በሕይወት ይኖራል።

20 መሞት የሚገባት ኀጢአት የሠራችው ነፍስ ናት። ልጅ በአባቱ ኀጢአት አይቀጣም፤ አባትም በልጁ ኀጢአት አይቀጣም። ጻድቁ የጽድቁን ፍሬ ያገኛል፤ ኀጢአተኛውም የኀጢአቱን ዋጋ ይቀበላል።

21 “ኀጢአተኛ ከሠራው ኀጢአት ሁሉ ተመልሶ ሥርዐቴን ሁሉ ቢጠብቅ፣ ቀናና ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።

22 በደሉ ሁሉ አይታሰብበትም፤ በጽድቅ መንገድ ሄዶአልና በሕይወት ይኖራል።

23 በውኑ ኀጢአተኛ ሲሞት ደስ ይለኛልን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ይልቁን ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ሲኖር ደስ አይለኝምን?

24 “ጻድቅ ሰው ግን ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ፣ ኀጢአተኛው የሚያደርገውንም አስጸያፊ ነገር ቢፈጽም፤ ይህ ሰው በውኑ በሕይወት ይኖራልን? ከሠራው ጽድቅ አንዱም አይታሰብለትም፤ ታማኝ ባለመሆኑና ከፈጸመው ኀጢአት የተነሣ ይሞታል።

25 “እናንተ ግን፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስማ፤ መንገዴ ቀና አይደለችምን? ቀና ያልሆነውስ የእናንተ መንገድ አይደለምን?

26 ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ በኀጢአቱ ይሞታል፤ ከፈጸመውም በደል የተነሣ በሕይወት አይኖርም።

27 ኀጢአተኛው ግን ከክፉ ሥራው ተመልሶ በታማኝነትና በቅንነት ቢኖር ሕይወቱን ያድናል።

28 የፈጸመውን በደል ሁሉ ተገንዝቦ ካደረገው ክፋት ሁሉ ስለ ተመለሰ፣ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።

29 የእስራኤል ቤት ግን፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ! መንገዴ ቀና አይደለችምን? ቀና ያልሆነችውስ የእናንተ መንገድ አይደለችምን?

30 “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለዚህ እንደየ ሥራችሁ በእያንዳንዳችሁ ላይ እፈርዳለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንግዲህ ንስሓ ግቡ በኀጢአት እንዳትጠፉ፣ ከኀጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።

31 በእኔ ላይ የፈጸማችሁትን በደል ሁሉ ወደ ኋላ ጣሉት፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ይኑራችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?

32 ማንም እንዲሞት አልሻምና፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ወደ እኔ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ!

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48