ሕዝቅኤል
ምዕራፎች 3
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
1እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በፊትህ ያለውን ብላ፤ ይህን ጥቅልል መጽሐፍ ብላና ሄደህ ለእስራኤል ቤት ተናገር” አለኝ።
2ስለዚህ አፌን ከፈትሁ፤ እርሱም መጽሐፉን አጐረሠኝ።
3እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እኔ የምሰጥህን ይህን ጥቅል መጽሐፍ ብላ፤ ሆድህንም ሙላ” አለኝ። እኔም በላሁት፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠኝ።
4እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፤ ቃሌንም ንገራቸው።
5ወደ እስራኤል ቤት እንጂ፣ ንግግሩ ወደማይገባና ቋንቋው ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህም፤
6ንግግራቸው ወደማይገባና ቋንቋቸው ወደማይታወቅ፣ ቃላቸውንም መረዳት ወደማይቻልህ ብዙ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነርሱ ልኬህ ቢሆን ኖሮ፣ በእርግጥ ይሰሙህ ነበር።
7ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ ልበ ደንዳኖችና እልኸኞች ስለሆኑ ሊሰሙኝ አልፈለጉም፤ ስለዚህ የእስራኤል ቤት አንተንም አይሰሙህም።
8እነሆ እኔ በእነርሱ ፊት የማትበገር ጠንካራ አደርግሃለሁ።
9ግንባርህን ከባልጩት ይልቅ እንደሚጠነክር ድንጋይ አደርገዋለሁ። ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም እንኳ አትፍራቸው፤ በፊታቸውም አትሸበር።”
10እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የምነግርህን ቃል ሁሉ በጥንቃቄ አድምጥ፤ በልብህም ያዝ።
11ተነሥተህም በምርኮ ወዳሉት ወገኖችህ ሄደህ ተናገራቸው፤ ቢሰሙህም ባይሰሙህም፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ በላቸው።”
12መንፈስም ወደ ላይ ከፍ አድርጎ አነሣኝ፤ ከኋላዬም ‘የእግዚአብሔር ክብር በማደሪያ ስፍራው ይባረክ!’ የሚል ታላቅ ህምህምታ ሰማሁ፤
13ይህም የሕያዋኑ ፍጡራን ክንፎች እርስ በርስ ሲጋጩና በአጠገባቸው ያሉት መንኰራኲሮች የሚያሰሙት ታላቅ ህምህምታ ነበር።
14መንፈስ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ወሰደኝ፤ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ቊጣ ሄድሁ፤ የእግዚአብሔርም ጽኑ እጅ በላዬ ነበረች።
15ከዚያም በኮቦር ወንዝ አጠገብ በቴልአቢብ ወደሚኖሩት ምርኮኞች መጣሁ፣ በድንጋጤ ፈዝዤም ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን በመካከላቸው ተቀመጥሁ።