1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ የወይን ግንድ በዱር ካሉት ዛፎች ሁሉ ቅርንጫፍ የሚሻለው በምንድን ነው?
3 የሚጠቅም ነገር ለመሥራት ከግንዱ አንዳች ተወስዶ ያውቃልን? ዕቃ የሚንጠለጠልበትስ ኵላብ ከእርሱ ይበጃልን?
4 እንዲነድ እሳት ላይ ከተጣለ በኋላ፣ እሳቱ ጫፍና ጫፉን አቃጥሎ፣ መኻሉን ከለበለበው፣ ለአንዳች ነገር ይጠቅማልን?
5 እንግዲህ ደኅና ሆኖ ሳለ ለምንም ነገር ካልጠቀመ፣ እሳት ካቃጠለውና ከለበለበው በኋላ ረብ የለሽነቱ የቱን ያህል የባሰ ይሆን!
6 “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከዱር ዛፎች መካከል የወይን ግንድ እንዲነድ ለእሳት አሳልፌ እንደ ሰጠሁ፣ እንዲሁ የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች አሳልፌ እሰጣለሁ።
7 ፊቴን በክፋት ወደ እነርሱ እመልሳለሁ፤ ከእሳት ቢያመልጡም፣ ገና እሳት ይበላቸዋል። ፊቴን በክፋት ወደ እነርሱ በመለስሁ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
8 ታማኝ ካለመሆናችሁ የተነሣ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”