1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለጢሮስ ገዥ እንዲህ በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ልብህ በትዕቢት ተወጥሮ፣“እኔ አምላክ ነኝ፤በአምላክ ዙፋን ላይ፣በባሕሮችም ልብ ተቀምጫለሁ” አልህ።ምንም እንኳ እንደ አምላክ ጠቢብ ነኝ ብለህ ብታስብም፣አንተ ሰው እንጂ አምላክ አይደለህም።
3 ከዳንኤል ይልቅ ጠቢብ ነህን?ከአንተስ የተሰወረ ምስጢር የለምን?
4 በጥበብህና በማስተዋልህ፣የራስህን ሀብት አከማቸህ፤ወርቅም ብርም፣በግምጃ ቤትህ አጠራቀምህ።
5 በንግድ ሥራ እጅግ ከመራቀቅህ የተነሣ፣በሀብት ላይ ሀብት አካበትህ፤ከሀብትህ ብዛት የተነሣም፤ልብህ በትዕቢት ተወጠረ።
6 “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘እንደ አምላክ ጥበበኛ ነኝ፤ ብለህስለምታስብ፣
7 ከአሕዛብ መካከል እጅግ ጨካኞች የሆኑትን ባዕዳን፣በአንተ ላይ አመጣለሁ፤በጥበብህ ውበት ላይ ሰይፋቸውን ይመዛሉ፤ታላቅ ክብርህንም ያረክሳሉ።
8 ወደ ጒድጓድ ያወርዱሃል፤በጥልቁም ባሕር ውስጥ፣በባሕሮችም ልብ ውስጥ አስከፊ ሞት ትሞታለህ።
9 ታዲያ በገዳዮችህ ፊት፣“አምላክ ነኝ” ትላለህን?በገዳዮችህ እጅ ስትገባ፣አንተ ሰው እንጂ አምላክ አይደለህም።
10 በባዕዳን እጅ፣ያልተገረዙትን ሰዎች አሟሟት ትሞታለህ፤እኔ ተናግሬአለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”
11 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
12 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ስለ ጢሮስ ንጉሥ ሙሾ አውርድ፤ እንዲህም በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ጥበብን የተሞላህ፣ ፍጹም ውበትን የተላበስህ፣የፍጹምነት ምሳሌ ነበርህ።
13 በእግዚአብሔር የአትክልት ቦታ፣በዔድን ነበርህ፤እያንዳንዱ የከበረ ድንጋይ አስጊጦህ ነበር፤ሰርድዮን፣ ቶጳዝዮን፣ አልማዝ፣መረግድ፣ ኢያሰጲድ፣ ሰንፔር፣በሉር፣ ቢረሌና የከበረ ዕንቍ።ልብስህም የሚያብረቀርቅ ዕንቍ ወርቅ ነበር፤የተዘጋጁትም አንተ በተፈጠርህበት ዕለት ነበር።
14 ጠባቂ ኪሩብ ሆነህ ተቀብተህ ነበር፤ለዚሁም ሾምሁህ፤በእግዚአብሔር ቅዱስ ተራራ ላይ ነበርህ፤በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ።
15 ከተፈጠርህበት ቀን ጀምሮ፣ክፋት እስከ ተገኘብህ ድረስ፣በመንገድህ ነቀፌታ አልነበረብህም።
16 ንግድህ ስለ ደረጀ፣በዐመፅ ተሞላህ፣ኀጢአትም ሠራህ፤ስለዚህ ከእግዚአብሔር ተራራ በውርደት አሳደድሁህ፤ጠባቂ ኪሩብ ሆይ፤ ከእሳት ድንጋዮችመካከል አስወጣሁህ።
17 በውበትህ ምክንያት፣ልብህ ታበየ፤ከክብርህ ታላቅነት የተነሣም፣ጥበብህን አረከስህ።ስለዚህ ወደ ምድር ወረወርሁህ፤ለነገሥታት ትዕይንት አደረግሁህ።
18 በኀጢአትህና በተጭበረበረው ንግድህ ብዛት፣መቅደስህን አረከስህ።ስለዚህ እሳት ከአንተ እንዲወጣ አደረግሁ፤እርሱም በላህ፤በሚመለከቱህ ሁሉ ፊት፣በምድር ላይ ዐመድ አደረግሁህ።
19 የሚያውቁህን አሕዛብ ሁሉ፣ሁኔታህ አስደንግጦአቸዋል፤መጨረሻህ የሚያሳዝን ሆነ፤ከእንግዲህ ሕልውና የለህም።
20 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
21 “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ሲዶና አዙር፤ ትንቢትም ተናገርባት፤
22 እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ሲዶን ሆይ፤ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤በውስጥሽ እከብራለሁ፤ቅጣትን ሳመጣባት፣ቅድስናዬንም በውስጧ ስገልጥ፣እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።
23 በእርሷ ላይ መቅሠፍት አመጣለሁ፤በመንገዶቿ ላይ ደም እንዲፈስ አደርጋለሁ፤ከየአቅጣጫው በሚመጣ ሰይፍ፣የታረዱት በውስጧ ይወድቃሉ፤ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።
24 “ ‘ከእንግዲህ ወዲያ የእስራኤል ሕዝብ የሚያሠቃይ አሜከላና የሚወጋ እሾኽ የሆኑ ጎረቤቶች አይኖሯቸውም፤ ከዚያም እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።
25 “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤልን ሕዝብ ከተበተኑባቸው አገሮች መካከል በምሰበስብበት ጊዜ፣ አሕዛብ እያዩ ቅድስናዬን በመካከላቸው እገልጣለሁ፤ ከዚያም በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ፤ ይህም ለባሪያዬ ለያዕቆብ የሰጠሁት ነው።
26 በዚያም በሰላም ይኖራሉ፤ ቤቶች ይሠራሉ፤ የወይን ተክል ቦታም ያበጃሉ። ያጣጣሏቸው ጎረቤቶቻቸውን ሁሉ በምቀጣበት ጊዜ እነርሱ በሰላም ይኖራሉ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ።’ ”