1 በተሰደድን በሃያ አምስተኛው ዓመት፣ በዓመቱ መጀመሪያ፣ በዐሥረኛው ቀን፣ ከተማዪቱ በወደቀች በዐሥራ አራተኛው ዓመት፣ በዚያው ዕለት የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ነበር፤ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ።
2 በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ፤ ከፍ ባለ ተራራ ላይ አኖረኝ፤ ከተራራውም በስተ ደቡብ፣ ከተማ የሚመስሉ ሕንጻዎች ነበሩ።
3 ወደዚያ ወሰደኝ፤ እነሆ መልኩ ናስ የሚመስል ሰው አየሁ፤ እርሱም የሐር ገመድና መለኪያ ዘንግ በእጁ ይዞ በመግቢያው በር ላይ ቆሞ ነበር።
4 ሰውየውም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በዐይንህ እይ፤ በጆሮህ ስማ፤ የማሳይህንም ሁሉ ልብ ብለህ አስተውል፤ ወደዚህ የመጣኸው ለዚህ ነውና ያየኸውንም ሁሉ ለእስራኤል ቤት ንገር።”
5 የቤተ መቅደሱን ዙሪያ ሙሉ በሙሉ የከበበ ቅጥር አየሁ፤ በሰውየውም እጅ ርዝመቱ ስድስት ክንድ የሆነ መለኪያ ዘንግ አየሁ፤ እያንዳንዱ ክንድ፣ አንድ ክንድ ከስንዝር ነበር፤ እርሱም ቅጥሩን ለካው፤ ስፋቱ አንድ መለኪያ ዘንግ ሲሆን፣ ቁመቱም እንዲሁ አንድ መለኪያ ዘንግ ነበር።
6 ከዚያም በምሥራቅ ትይዩ ወዳለው በር መጣ፤ ደረጃዎቹን ወጥቶ የበሩን መግቢያ መድረክ ለካ፤ ቍመቱም አንድ ዘንግ ነበር።
7 የዘብ ጠባቂ ቤቶች፣ ቁመታቸው አንድ መለኪያ ዘንግ፣ ወርዳቸውም አንድ መለኪያ ዘንግ ነበር፤ በቤቶቹም መካከል ያሉት ግንቦች ውፍረት አምስት ክንድ ነበር። ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ባለው መተላለፊያ በረንዳ አጠገብ በውስጥ በኩል ያለው የበሩ መድረክ ወለል አንድ ዘንግ ነበር።
8 ከዚያም የመግቢያውን በር መተላለፊያውን በረንዳ ለካ፤
9 ቍመቱ ስምንት ክንድ፣ የዐምዶቹም ውፍረት ሁለት ክንድ ነበር። የመግቢያው በር መተላለፊያ በረንዳ፣ ከቤተ መቅደሱ ትይዩ ነው።
10 በምሥራቁ በር ግራና ቀኝ መጠናቸው እኩል የሆነ ሦስት ሦስት የዘብ ቤቶች ነበሩ፤በመካከላቸው ወጣ ወጣ ብለው የሚታዩትም ግንቦች ተመሳሳይና እኩል ነበሩ።
11 ከዚያም የበሩን ስፋት ለካ፤ ወርዱ ዐሥር ክንድ፣ ርዝመቱም ዐሥራ ሦስት ክንድ ነበር።
12 በእያንዳንዱ ዘብ ቤት ፊት ለፊት ከፍታው አንድ ክንድ የሆነ መከለያ የግንብ ዐጥር አለ፤ የዘብ ቤቶቹም ስፋት እኩል በኩል ስድስት ክንድ ነበር።
13 ከዚያም ከዘብ ቤቱ የኋላ ግድግዳ ጀምሮ እስከ ሌላው ጫፍ ድረስ ያለውን የመግቢያ በር ለካ፤ ከአንዱ መከለያ ግድግዳ እስከ ሌላው መከለያ ግድግዳ ያለው ርቀት ሃያ አምስት ክንድ ነበር።
14 በመግቢያው በር ዙሪያ ባሉት ወጣ ወጣ ባሉት ግንቦች ሁሉ ፊት ለፊት ያለውን ቦታ ለካ፤ ሥልሳ ክንድም ነበር። የተለካውም ከአደባባዩ ፊት ለፊት እስካለው መተላለፊያ በረንዳ ድረስ ነበር።
15 ከበሩ መግቢያ እስከ መተላለፊያ በረንዳው መጨረሻ ድረስ ያለው ርቀት አምሳ ክንድ ነበር።
16 ክፍሎቹ እንደ መተላለፊያ በረንዳዎቹ ከግራና ከቀኝ በኩል ትንንሽ መስኮቶች አሏቸው። በዙሪያው ያሉ መስኮቶች በመግቢያው በር ፊት ለፊት የነበሩ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ክፍል ግራና ቀኝ ግድግዳ ላይ ደግሞ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾበታል።
17 ከዚያም ወደ ውጩ አደባባይ አመጣኝ፤ እዚያም በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ክፍሎችና ድንጋይ የተነጠፈበት መመላለሻ አየሁ፤ በመመላለሻውም ዙሪያ ሠላሳ ክፍሎች ነበሩ።
18 የታችኛው ንጣፍ ወለል ከመግቢያው በር ጋር ተያይዞ የተሠራ ሲሆን፣ ስፋቱ እንደ በሮቹ ርዝመት መጠን ነበር።
19 ከዚያም ከታችኛው መግቢያ በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ያለውን ርቀት ለካ፤ በምሥራቅም ሆነ በሰሜን በኩል ያለው ርቀት አንድ መቶ ክንድ ነበር።
20 ከዚያም በሰሜን ትይዩ ያለውን፣ ወደ ውጩ አደባባይ የሚያመራውን በር ርዝመትና ወርድ ለካ።
21 እንደ መጀመሪያው በር ሁሉ ይኸኛውም በየጐኑ ያሉት ሦስት ሦስት የዘብ ቤቶች፣ በየመካከሉ ወጣ ወጣ ያሉ ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው እኩል ነበር። ርዝመቱ አምሳ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።
22 መስኮቶቹ፣ መተላለፊያ በረንዳዎቹና የዘንባባ ዛፍ ቅርጾቹ ልካቸው በምሥራቁ በር ካሉት ጋር ተመሳሳይ ነበር። ወደዚያ የሚያመሩ ሰባት ደረጃዎች አሉ፤ መተላለፊያ በረንዳዎቹም ከእነርሱ ጋር ትይዩ ነበር።
23 ልክ በምሥራቅ በኩል እንዳለው ሁሉ፣ ከሰሜኑ በር ጋር ትይዩ የሆነ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያመራ በር አለ። ከአንዱ በር እስከ ሌላኛው በር ያለውን ለካው፤ ይህም አንድ መቶ ክንድ ነበር።
24 ከዚያም ወደ ደቡብ አቅጣጫ መራኝ፤ እዚያም ፊቱን ወደ ደቡብ ያደረገ በር አየሁ፤ እርሱም የውስጠኛውን ግድግዳና መተላለፊያ በረንዳውን ለካ፤ የእነዚህም መጠን እንደ ሌሎቹ በሮች ነበር።
25 የመግቢያው በርና መተላለፊያ በረንዳው እንደ ሌሎቹ ሁሉ በዙሪያው ጠባብ መስኮቶች ነበሩት፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ፤ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።
26 ከመተላለፊያ በረንዳው ትይዩ የሆኑ ሰባት ደረጃዎች ወደ መግቢያው በር ያመራሉ፤ ወጣ ወጣ ብለው በሚታዩ ግድግዳዎችም ላይ የዘንባባ ቅርጽ አለ።
27 ውስጠኛው አደባባይ ደግሞ ከደቡብ ጋር ትይዩ የሆነ በር አለው፤ እርሱም ከዚህ በር አንሥቶ በደቡብ አቅጣጫ እስካለው እስከ ውጭው በር ድረስ ለካው፤ ይህም አንድ መቶ ክንድ ሆነ።
28 ከዚያም በደቡብ በር በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ የደቡብንም በር ለካው፤ መጠኑም እንደ ሌሎቹ በሮች ነበር።
29 የዘብ ቤቶቹ፣ በየመካከሉ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር። መግቢያው በርና መተላለፊያ በረንዳዎቹ በዙሪያቸው መስኮቶች ነበሯቸው። ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።
30 በውስጠኛው አደባባይ ዙሪያ ያሉት የመግቢያው በር መተላለፊያ በረንዳዎቹ ርዝመት ሃያ አምስት ክንድ ሲሆን፣ ወርዳቸው ደግሞ አምስት ክንድ ነበር።
31 መተላለፊያ በረንዳው ከውጭው አደባባይ ጋር ትይዩ ነው፤ የዘምባባ ዛፎች በዐምዶቹ ላይ ተቀርጸዋል፤ እስከ መግቢያው ድረስም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
32 ከዚያም በምሥራቅ በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ መግቢያ በሩንም ለካው፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር።
33 የዘብ ቤቶቹ፣ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር፤ መግቢያው በርና መተላለፊያ በረንዳው ዙሪያውን መስኮቶች ነበሩት፤ የዚህም ርዝመቱ አምሳ ክንድ፣ ወርዱ ሃያ አምስት ክንድ ነበር።
34 መተላለፊያ በረንዳው ከውጩ አደባባይ ትይዩ ነው፤ በዐምዶቹ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾአል፤ እስከ መግቢያ ድረስም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
35 ከዚያም ወደ ሰሜን በር አመጣኝ፤ ለካውም፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር።
36 የዘብ ቤቶቹ፣ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦቹና መተላለፊያ በረንዳው መጠናቸው ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር፤ በዙሪያውም መስኮቶች ነበሩት። የዚህም ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።
37 መተላለፊያ በረንዳው ከውጩ አደባባይ ትይዩ ነው፤ በዐምዶቹም ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾአል፤ እስከ መግቢያው ድረስም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
38 በእያንዳንዱ የውስጥ መግቢያ በር መተላለፊያ በረንዳ አጠገብ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚታጠብበት በር ያለው ክፍል አለ።
39 በመግቢያው በር ላይ ባለው መተላለፊያ በረንዳው ሥር በግራና በቀኝ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የኀጢአትና የበደል መሥዋዕት የሚታረዱበት ሁለት ሁለት ጠረጴዛዎች አሉ።
40 ከመግቢያው በር ላይ ባለው መተላለፊያ በረንዳ በስተ ውጭው ግንብ ወደ ሰሜን በር መግቢያ ላይ ባሉት ደረጃዎች አጠገብ ከግራና ከቀኝ ሁለት ሁለት ጠረጴዛዎች ይገኛሉ።
41 ስለዚህ በአንዱ በር በኩል አራት፣ በሌላውም በኩል አራት ጠረጴዛዎች፤ መሥዋዕቱ የሚታረድባቸው በድምሩ ስምንት ጠረጴዛዎች አሉ ማለት ነው።
42 ለሚቃጠለው መሥዋዕት መገልገያ የሆኑ፣ ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ አራት ጠረጴዛዎች ነበሩ፤ የእያንዳንዳቸው ርዝመት፣ ወርድና ቁመት አንድ ክንድ ተኩል ነበር፤ በእነዚህም ላይ ለሚቃጠለው መሥዋዕትና ለሌላውም መሥዋዕት ማረጃ የሚሆኑ መሣሪያዎች ይቀመጡባቸው ነበር።
43 እንዲሁም አንዳንድ ስንዝር የሚሆኑ ሁለት ጣት ያላቸው ሜንጦዎች በግንቡ ዙሪያ ተንጠልጥለው ነበር፤ ጠረጴዛዎቹም የመሥዋዕቱ ሥጋ ማስቀመጫ ነበሩ።
44 በውስጠኛው አደባባይ፣ ከውስጠኛው በር ውጭ፣ ሁለት ክፍሎች ነበሩ፤ አንዱ በደቡብ ትይዩ በሰሜን በር በኩል ሲሆን፣ ሌላው በሰሜን ትይዩ በደቡብ በር በኩል ነበር።
45 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “በደቡብ ትይዩ ያለው ክፍል በቤተ መቅደስ ውስጥ ለሚያገለግሉ ካህናት ሲሆን፣
46 በሰሜን ትይዩ ያለው ክፍል ደግሞ በመሠዊያው ላይ ለሚያገለግሉ ካህናት ነው። እነዚህም የሳዶቅ ልጆች ሲሆኑ፣ በእግዚአብሔር ፊት ቀርበው ማገልገል የሚችሉ ሌዋውያን እነርሱ ብቻ ናቸው።”
47 ከዚያም አደባባዩን ለካው፤ ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ፣ ወርዱ መቶ ክንድ እኩል በእኩል ባለ አራት ማእዘን ነበር። መሠዊያውም በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ነበር።
48 ወደ ቤተ መቅደሱም መተላለፊያ በረንዳ አመጣኝ፤ የመተላለፊያ በረንዳዎቹን ዐምዶች ለካ፤ በአንዱ በኩል አምስት ክንድ በሌላውም እንዲሁ አምስት ክንድ ነበር። የመግቢያው በር ርዝመት ዐሥራ አራት ክንድ ሲሆን፣ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦች ስፋት በአንዱ በኩል ሦስት ክንድ፣ በሌላውም እንዲሁ ሦስት ክንድ ነበሩ።
49 የመተላለፊያው በረንዳ ርዝመት ሃያ ክንድ፣ ከፊት እስከ ኋላ ያለውም ወርድ ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበር። ወደ ቤተ መቅደሱም የሚያደርሱ ዐሥር ደረጃዎች የነበሩ ሲሆን፣ በየዐምዱም ጐንና ጐን ምሰሶዎች ነበሩ።