1 “አንተ የሰው ልጅ ሆይ፤ በጎግ ላይ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሞሳሕና የቶቤል ዋና አለቃ ጎግ ሆይ፤ ተነሥቼብሃለሁ፤
2 ወደ ኋላ እመልስሃለሁ፤ እንዲሁም እጐትትሃለሁ፤ ከሩቅ ሰሜን አምጥቼ በእስራኤል ተራሮች ላይ እሰድሃለሁ።
3 በግራ እጅህ ያለውን ቀስትህን እመታለሁ፤ በቀኝ እጅህ የያዝሃቸውንም ፍላጾች አስረግፍሃለሁ።
4 አንተና ወታደሮችህ ሁሉ፣ ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝቦች በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ። ነጣቂ አሞሮችና የዱር አራዊት ይበሏችሁ ዘንድ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ።
5 አውላላ ሜዳ ላይ ትወድቃለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
6 በማጎግና ያለ ሥጋት በባሕር ዳርቻ በሚኖሩት ላይ እሳት እሰዳለሁ፤ እነርሱም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።”
7 “ ‘ቅዱሱ ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል ዘንድ እንዲታወቅ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ቅዱስ ስሜ እንዲናቅ፣ እንዲቃለል አልፈልግም፤ አሕዛብም እኔ እግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ እንደሆንሁ ያውቃሉ።
8 እነሆ ይመጣል፤ በእርግጥም ይሆናል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያ ያልሁት ቀን ይህ ነው።
9 “ ‘ከዚያም በእስራኤል ከተሞች የሚኖሩ ሁሉ ወጥተው የጦር መሣሪያውን፣ ትልልቁንና ትንንሹን ጋሻ፣ ቀስቱን፣ ፍላጻውን፣ የጦር ዱላውንና ጦሩን ሰብስበው ማገዶ በማድረግ ያነዱታል፤ ሰባት ዓመት ይማግዱታል።
10 ከሜዳ ላይ ዕንጨት መልቀም፣ ከዱርም ዛፍ መቍረጥ አያስፈልጋቸውም፤ የጦር መሣሪያቸውን በመማገድ ይጠቀማሉና። የዘረፏቸውን ይዘርፋሉ፤ የበዘበዟቸውን ይበዘብዛሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
11 “ ‘በዚያ ቀን ሰዎች በምሥራቅ በኩል ወደ ባሕሩ በሚጓዙበት ሸለቆ፣ ለጎግ የመቃብር ስፍራ በእስራኤል እሰጠዋለሁ። ጎግና ሰራዊቱ ሁሉ በዚያ ስለሚቀበሩ፣ የተጓዦችን መንገድ ይዘጋሉ፤ ስለዚህም የሐሞን ጎግ ሸለቆ ይባላል።
12 “ ‘ምድሪቱን ለማጽዳት፣ የእስራኤል ቤት ሰዎች ሰባት ወር ሙሉ ይቀብሯቸዋል።
13 የምድሪቱ ሰዎች ሁሉ ይቀብሯቸዋል፤ እኔ የምከብርበትም ዕለት የመታሰቢያ ቀን ይሆናቸዋል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
14 “ ‘ሰዎች ምድሪቱን ለማጽዳት በየጊዜው ይቀጠራሉ። አንዳንዶቹ ምድሪቱን ያስሳሉ፤ ከእነርሱም በተጨማሪ ሌሎች ሳይቀበሩ የቀሩትን ይቀብራሉ። ከሰባት ወር በኋላም ፍለጋ ይጀምራሉ።
15 እነርሱም በምድሪቱ መካከል ሲሄዱ፣ ከእነርሱ አንዱ የሰው ዐፅም ባየ ቍጥር ምልክት ያደርግበታል፤ ይህም መቃብር ቈፋሪዎች በሐሞን ጎግ ሸለቆ እስኪቀብሩት ድረስ ነው።
16 በዚያም ሐሞና የምትባል ከተማ አለች፤ ስለዚህ ምድሯን ያጸዳሉ።’
17 “ ‘የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ማንኛውንም ዐይነት ወፍና የዱር አራዊት ሁሉ ጥራ፤ እንዲህም በላቸው፤ “ከየአቅጣጫው ተሰብስባችሁ እኔ ወደማዘጋጅላችሁ መሥዋዕት ኑ፤ ይህም በእስራኤል ተራሮች ላይ የሚሆን ታላቁ መሥዋዕት ነው። በዚያ ሥጋ ትበላላችሁ፤ ደምም ትጠጣላችሁ።
18 እንደ አውራ በግና እንደ ጠቦት፤ እንደ ፍየልና እንደ ወይፈን፣ የኀያላን ሰዎችን ሥጋ ትበላላችሁ፤ የምድርንም መሳፍንት ደም ትጠጣላችሁ፤ እነዚህ ሁሉ የሰቡ የባሳን ከብቶች ናቸው።
19 እኔ በማዘጋጅላችሁም መሥዋዕት እስክትጠግቡ ስብ ትበላላችሁ፤ እስክትሰክሩም ደም ትጠጣላችሁ።
20 በገበታዬም ፈረሶችንና ፈረሰኞችን፣ ኀያላን ሰዎችንና ከየወገኑ የሆኑትን ወታደሮች እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’
21 “ክብሬን በአሕዛብ መካከል እገልጣለሁ፤ አሕዛብም ሁሉ በእነርሱ ላይ ያመጣሁትን ቅጣትና በላያቸው ላይ የጫንሁትን እጅ ያያሉ።
22 ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር፣ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ።
23 አሕዛብም የእስራኤል ሕዝብ ለእኔ ታማኞች ባለመሆን ከሠሩት ኀጢአት የተነሣ እንደ ተሰደዱ ያውቃሉ፤ ስለዚህ ፊቴን ከእነርሱ ሰወርሁ፤ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ ሰጠኋቸው፤ ሁሉም በሰይፍ ወደቁ።
24 እንደ ርኵሰታቸውና እንደ በደላቸው መጠን ፈረድሁባቸው፤ ፊቴንም ከእነርሱ ሰወርሁ።
25 “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ያዕቆብን አሁን ከስደት እመልሰዋለሁ፤ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እራራለሁ፤ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ።
26 የሚያስፈራቸው ማንም ሳይኖር በምድራቸው በሰላም በሚኖሩበት ጊዜ፣ ውርደታቸውንና ለእኔ ታማኝ ሆነው ያልኖሩበትን ዘመን ይረሳሉ።
27 ከአሕዛብ ምድር መልሼ ሳመጣቸው፣ ከጠላቶቻቸው አገር ስሰበስባቸው የራሴን ቅድስና በእነርሱ በኩል በብዙ ሕዝቦች ፊት አሳያለሁ።
28 በአሕዛብ መካከል እንዲሰደዱ ባደርግም፣ አንድም ሳላስቀር ወደ ገዛ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ።
29 ከእንግዲህ ፊቴን ከእነርሱ አልሰውርም፤ መንፈሴን በእስራኤል ቤት ላይ አፈሳለሁና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”