ሕዝቅኤል

ምዕራፎች 21

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

የቅጣት በትር የሆነችው ባቢሎን

1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም አዙር፤ በመቅደሱ ላይ ቃል ተናገር፤ በእስራኤል ምድር ላይ ትንቢት ተንብይ፤ 3እንዲህም በል፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ሰይፌን ከሰገባው እመዛለሁ፤ ጻድቁንም፣ ክፉውንም ከአንተ ዘንድ አስወግዳለሁ። 4ጻድቁንም ክፉውንም ስለማስወ ግድ ሰይፌ ከደቡብ ጀምሮ እስከ ሰሜን ባለው ሕዝብ ሁሉ ላይ ከሰገባው ይመዘዛል። 5ሰይፌን ከሰገባው የመዘዝሁት እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ሕዝቡ ሁሉ ያውቃል፤ እርሱም ወደ ሰገባው አይመለስም።’ 6“ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ አቃስት፤ በተሰበረ ልብና በመረረ ሐዘን አቃስት፤ 7እነርሱም፣ ‘ለምን ታቃስታለህ?’ ቢሉህ፣ “ስለሚመጣው ክፉ ወሬ ነው፤ ልብ ሁሉ ይቀልጣል፤ እጅም ሁሉ ይዝላል፤ ነፍስ ሁሉ ይደክማል፤ ጒልበትም ሁሉ ውሃ ይሆናል’ በላቸው። እነሆ ይመጣል፤ ይፈጸማልም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።” 8 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 9“የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ሰይፍ! ሰይፍ!የተሳለ የተወለወለም፤ 10የተሳለው ሊገድል፣የተወለወለውም እንደ መብረቅ ሊብረቀረቅ ነው!“ ‘ታዲያ፣ እንዴት ደስ ሊለን ይችላል? ሰይፉ የልጄን በትረ መንግሥት እንደ ማንኛውም በትር ንቆአል። 11“ ‘በእጁ እንዲያዝ፣ሰይፉ ሊወለወል ተሰጥቶአል፤ገዳዩ በእጁ እንዲጨብጠው፣ተስሎአል፤ ተወልውሎአል። 12የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህ በሕዝቤ ላይ፣በእስራኤልም መሳፍንት ሁሉ ላይ መጥቶአልና፤ጩኸት፣ ዋይታም አሰማ።እነርሱ ከሕዝቤ ጋር በአንድ ላይ፣ለሰይፍ ተጥለዋል፤ስለዚህ ደረትህን ምታ። 13“ ‘ፈተና በእርግጥ ይመጣል፤ ሰይፉ የናቀው በትረ መንግሥት ዘላቂነት ባይኖረውስ? ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ 14“እንግዲህ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤በእጅህም አጨብጭብ፤ሰይፉ ሁለት ጊዜ፣ሦስት ጊዜም ይምታ፤በእጅጉ የሚገድል፣ለግድያ የሚሆን፣በየአቅጣጫውም የሚከባቸው ሰይፍ ነው። 15ልብ ሁሉ ይቀልጥ ዘንድ፣የሚወድቁትም እንዲበዙ፣በበሮቻቸው ሁሉ፣የግድያውን ሰይፍ አኑሬአለሁ።ወዮ! እንዲያብረቀርቅ ተወልውሎአል፤ለመግደልም ተመዞአል። 16ሰይፍ ሆይ፤ በስለትህ አቅጣጫ ሁሉ፣ወደ ቀኝም፣ወደ ግራም ቍረጥ። 17እኔም በእጄ አጨበጭባለሁ፤ቍጣዬም ይበርዳል፤እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።” 18 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 19“የሰው ልጅ ሆይ፤ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ የሚመጣባቸውን የሁለት መንገዶች ካርታ ንደፍ፤ መንገዶቹም ከአንድ አገር የሚነሡ ናቸው፤ መንገዱ ወደ ከተማው በሚገነጠልበት ቦታ ላይ ምልክት አቁም። 20በአሞናውያን ከተማ በረባት ላይ ለሚመጣው ሰይፍ አንደኛውን መንገድ ምልክት አድርግ፤ በይሁዳና በተመሸገችው ከተማ በኢየሩሳሌም ላይ ለሚመጣውም ሰይፍ ሁለተኛውን መንገድ ምልክት አድርግ። 21የባቢሎን ንጉሥ በጥንቈላ ምሪት ለማግኘት በመንታ መንገድ ላይ በሁለቱ ጐዳናዎች መጋጠሚያ ላይ ይቆማል፤ ቀስቶቹን በመወዝወዝ ዕጣ ይጥላል፤ አማልክቱን ያማክራል፤ ጒበትንም ይመረምራል። 22የቅጥር መደርመሻ አምጥቶ እንዲያቆም፣ ለመግደል ትእዛዝ እንዲሰጥ፣ ፉከራ እንዲያሰማ፣ ቅጥር መደርመሻውን በከተሞች በር ላይ እንዲያደርግ፣ የዐፈር ድልድል እንዲያበጅና ምሽግ እንዲሠራ የኢየሩሳሌም ዕጣ በቀኝ እጁ ወጣ። 23ይህም ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ለገቡት የተሳሳተ ምሪት ይመስላል፤ እርሱ ግን በደላቸውን ያሳስባቸዋል፤ ማርኮም ይዞአቸው ይሄዳል። 24“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እናንተ በምታደርጉት ሁሉ ኀጢአታችሁን በመግለጽ፣ በግልጽም በማመፅ በደላችሁን ስላሳሰባችሁ፣ እንዲህም ስላደረጋችሁ በምርኮ ትወሰዳላችሁ። 25“ ‘አንተ የግፍ ጽዋህ የሞላ፣ የምትቀጣበት ቀን የደረሰ፣ ርኩስና ክፉ የእስራኤል መስፍን ሆይ፤ 26ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጥምጥምህን አውልቅ፤ ዘውድህን ጣል፤ እንደ ከዚህ በፊቱ አይሆንም፤ ዝቅ ያለው ከፍ ይላል፤ ከፍ ያለውም ዝቅ ይላል። 27ባድማ! ባድማ! ባድማ አደርጋታለሁ፤ የሚገባው ባለ መብት እስከሚመጣ ድረስ እንደ ቀድሞው አትሆንም፤ ለእርሱም ደግሞ እሰጣታለሁ።” ’ 28“አንተ የሰው ልጅ ሆይ! እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ስለ አሞናውያንና ስለ ስድባቸው ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ሰይፍ! ሰይፍ!ሊገድል የተመዘዘ፣ሊያጠፋ የተጠረገ፣እንደ መብረቅ ሊያብረቀርቅ የተወለወለ፤ 29የታለመልህ የሐሰት ራእይ፣የተነገረልህ የውሸት ሟርት ቢኖርም፣የግፍ ጽዋቸው በሞላ፣ቀናቸው በደረሰ፣መታረድ በሚገባቸው ክፉዎች፣አንገት ላይ ይሆናል። 30ሰይፉን ወደ ሰገባው መልሰው፤በተፈጠርህበት ምድር፣በተወለድህበትም አገር፣በዚያ እፈርድብሃለሁ። 31መዓቴን በላይህ አፈሳለሁ፤የቍጣዬንም እሳት አነድብሃለሁ፣በጥፋት ለተካኑ፣ለጨካኞች ሰዎች አሳልፌ እሰጥሃለሁ። 32ለእሳት ማገዶ ትሆናለህ፣ደምህ በምድርህ ይፈሳል፣ከእንግዲህ መታሰቢያ አይኖርህም፤እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና።’ ”