ሕዝቅኤል 42 NASV

ለካህናት የተመደቡ ክፍሎች

1 ከዚያም ያ ሰው በሰሜን በኩል ወዳለው ወደ ውጩ አደባባይ በማምጣት፣ በቤተ መቅደሱ አደባባይ ትይዩና በሰሜን በኩል ባለው ግንብ ትይዩ ወደ አሉት ክፍሎች አመጣኝ።

2 በሩ በሰሜን ትይዩ የሆነው ሕንጻ ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ ወርዱም አምሳ ክንድ ነበር።

3 ከውስጠኛው አደባባይ ሃያ ክንድ ርቀት ላይና በአንጻሩም ከውጩ አደባባይ የንጣፍ ድንጋይ ፊት ለፊት ርቀት ላይ በሦስት ደርቦች ትይዩ የሆኑ ሰገነቶች ነበሩ።

4 ከክፍሎቹ ፊት ለፊት ወርዱ ዐሥር ክንድ፣ ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ የሆነ መተላለፊያ በውስጥ በኩል ነበር። የክፍሎቹም በሮች በሰሜን በኩል ነበሩ።

5 የላይኞቹ ክፍሎች ጠበብ ያሉ ናቸው፤ ምክንያቱም ሰገነቶቹ ታችና መካከል ላይ ካሉት ከሕንጻው ክፍሎች ይልቅ ሰፋ ያሉ ቦታዎች ይዘውባቸዋልና።

6 አደባባዮቹ ዐምዶች ሲኖሯቸው፣ በሦስተኛው ደርብ ላይ ያሉት ክፍሎች ግን ዐምድ የላቸውም። ስለዚህ የወለላቸው ስፋት በታችኛውና በመካከለኛው ደርብ ካሉት ክፍሎች ይልቅ ጠበብ ያለ ነው።

7 ከክፍሎቹና፣ ከውጩ አደባባይ ትይዩ የሆነ የውጪ ግንብ አለ፤ ይህም በክፍሎቹ ፊት ለፊት ሆኖ አምሳ ክንድ ይረዝማል።

8 ከውጩ አደባባይ ቀጥሎ ያሉት መደዳ ክፍሎች ርዝመት አምሳ ክንድ ሲሆን፣ ከቤተ መቅደሱ አጠገብ ያሉት መደዳ ክፍሎች ርዝመት ደግሞ አንድ መቶ ክንድ ነበር።

9 ከውጩ አደባባይ ወደ ውስጥ ሲገባ፣ በስተ ምሥራቅ የታችኞቹ ክፍሎች መግቢያ ይገኛል።

10 በደቡብ በኩል የውጩን አደባባይ ግንብ ተከትሎ፣ ከቤተ መቅደሱ አደባባይ ጋር የተያያዙና ከውጩ ግንብ ጋር ትይዩ የሆኑ ክፍሎች አሉ፤

11 ከፊት ለፊታቸውም መተላለፊያ መንገድ አለ። እነዚህ በሰሜን በኩል ካሉት ክፍሎች ጋር ተመሳሳይ ሲሆኑ፣ ርዝመትና ወርዳቸው፣ መውጫና መጠናቸው አንድ ዐይነት ነበር፤ በሰሜን በኩል እንዳሉት በሮች፣

12 በደቡብ በኩል ያሉት ክፍሎች በሮች መጠናቸው ተመሳሳይ ነበር። ከመመላለሻው መነሻ ላይ መግቢያ በር አለ፤ መመለሻውም ፊት ለፊት ካለው ወደ ምሥራቅ ከሚያመራው ግንብ ጋር ተጓዳኝ ነው።

13 ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “ከቤተ መቅደሱ አደባባይ ፊት ለፊት ያሉት የሰሜኑና የደቡቡ ክፍሎች የካህናቱ ሲሆኑ፣ እነዚህም በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርቡት ካህናት እጅግ የተቀደሱትን ቍርባኖች የሚበሉባቸው ናቸው። በዚያም እጅግ የተቀደሱትን ቍርባኖች ማለት የእህሉን ቍርባን፣ የኀጢአቱን ቍርባን፣ የበደሉን ቍርባን ያስቀምጣሉ፤ ቦታው ቅዱስ ነውና።

14 ካህናቱ አንድ ጊዜ ወደ ተቀደሰው ቦታ ከገቡ በኋላ፣ ያገለገሉበትን ልብስ ሳያወልቁ ወደ ውጩ አደባባይ መውጣት አይችሉም፤ የተቀደሰ ነውና፤ ወደ ሕዝቡ ቦታ ከመምጣታቸው በፊት ሌላውን ልብሳቸውን መልበስ አለባቸው።”

15 በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለውን ስፍራ ለክቶ ከጨረሰ በኋላ፣ በምሥራቅ በር በኩል ወደ ውጩ አወጣኝ፤ በዙሪያው ያለውንም ስፍራ ሁሉ ለካ፤

16 በምሥራቅ ያለውንም በመለኪያው ዘንግ ለካ፤ አምስት መቶ ክንድ ሆነ።

17 ሰሜኑንም ለካ፤ በመለኪያው ዘንግ አምስት መቶ ክንድ ሆነ።

18 ደቡቡንም ለካ፤ በመለኪያው ዘንግ አምስት መቶ ክንድ ሆነ።

19 ከዚያም ወደ ምዕራብ ጐን ዞሮ ለካ፤ በመለኪያው ዘንግ አምስት መቶ ክንድ ሆነ።

20 ስለዚህ በአራቱም ማእዘን ለካው፤ የተቀደሰውን ስፍራ ከሌላው የሚለይ በዙሪያው ግንብ ነበረ፤ የግንቡም ርዝመት አምስት መቶ ክንድ ሲሆን፣ ወርዱ አምስት መቶ ክንድ ነበር።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48