1 “አንተ የሰው ልጅ ሆይ፤ በጎግ ላይ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሞሳሕና የቶቤል ዋና አለቃ ጎግ ሆይ፤ ተነሥቼብሃለሁ፤
2 ወደ ኋላ እመልስሃለሁ፤ እንዲሁም እጐትትሃለሁ፤ ከሩቅ ሰሜን አምጥቼ በእስራኤል ተራሮች ላይ እሰድሃለሁ።
3 በግራ እጅህ ያለውን ቀስትህን እመታለሁ፤ በቀኝ እጅህ የያዝሃቸውንም ፍላጾች አስረግፍሃለሁ።
4 አንተና ወታደሮችህ ሁሉ፣ ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝቦች በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ። ነጣቂ አሞሮችና የዱር አራዊት ይበሏችሁ ዘንድ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ።