1 ስለ ግብፅ የተነገረ ንግር፤እነሆ፤ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ላይ ተቀምጦወደ ግብፅ ይመጣል፤የግብፅ ጣዖቶች በፊቱ ይርዳሉ፤የግብፃውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል።
2 “ግብፃዊውን በግብፃዊው ላይ አስነሣለሁ፤ወንድም ወንድሙን፣ባልንጀራ ባልንጀራውን፣ከተማም ከተማን፣መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል።
3 የግብፃውያን ልብ ይሰለባል፤ዕቅዳቸውንም መና አስቀራለሁ፤እነርሱም ጣዖታትንና የሙታንን መናፍስት፤መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ምክር ይጠይቃሉ።
4 ግብፃውያንን አሳልፌ፣ለጨካኝ ጌታ ክንድ እሰጣቸዋለሁ፤አስፈሪ ንጉሥም ይገዛቸዋል”ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
5 የዐባይ ወንዝ ይቀንሳል፤ውሃውም እየጐደለ ይሄዳል።
6 መስኖዎቹ ይከረፋሉ፤የግብፅ ጅረቶች ይጐድላሉ፤ ይጠፋሉም።ደንገሉና ቄጠማውም ይጠወልጋል፤
7 እንዲሁም በዐባይ ዳር፣በወንዙ መፋሰሻ ላይ ያሉት ተክሎች ይጠወልጋሉ።በዐባይ ዳር የተዘራው ዕርሻ ሁሉ፣በነፋስ ይወሰዳል፤ ምንም አይቀርም።