1 ዖፅ በሚባል አገር የሚኖር ኢዮብ የተባለ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ነበር።
2 እርሱም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ነበሩት።
3 ሀብቱም ሰባት ሺህ በጎች፣ ሦስት ሺህ ግመሎች፣ አምስት መቶ ጥማድ በሬዎችና አምስት መቶ እንስት አህዮች ነበረ፤ እጅግ ብዙ ባሮችም ነበሩት፤ በምሥራቅ አገር ከሚኖሩትም ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ታላቅ ሰው ነበረ።
4 ወንዶች ልጆቹም ተራ በተራ በየቤታቸው ግብዣ ያደርጉ ነበር፤ ከእነርሱም ጋር እንዲበሉና እንዲጠጡ ሦስቱን እኅቶቻቸውን ይጋብዙ ነበር።
5 የግብዣው ጊዜ ካለፈ በኋላ ኢዮብ ልኮ ያስመጣቸውና፣ “ምናልባት ልጆቼ ኀጢአት ሠርተው እግዚአብሔርንም በልባቸው ረግመው ይሆናል” በማለት ጠዋት በማለዳ ስለ እያንዳንዳቸው የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ ያነጻቸው ነበር፤ ኢዮብ ይህን ዘወትር ያደርግ ነበር።
6 አንድ ቀን መላእክት በእግዚአብሔር ፊት ሊቆሙ በመጡ ጊዜ፣ ሰይጣንም መጥቶ በመካከላቸው ቆመ።
7 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “ከወዴት መጣህ?” አለው።ሰይጣንም፣ “በምድር ሁሉ ዞርሁ፤ ወዲያና ወዲህም ተመላለስሁባት” ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ።
8 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው የለም” አለው።
9 ሰይጣንም፣ ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰለት፣ “ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራው እንዲሁ ነውን?
10 በእርሱና በቤተ ሰቦቹ፣ ባለው ንብረትስ ሁሉ ዙሪያ ዐጥር ሠርተህለት የለምን? የበጎቹና የላሞቹ መንጋ ምድርን ሁሉ እስኪሞሉ ድረስ የእጁን ሥራ ባርከህለታል።
11 እስቲ፣ እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ንካበት፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።”
12 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “እነሆ፤ እርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፤ እርሱን ራሱን ግን እንዳትነካው” አለው።ከዚህ በኋላ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄደ።
13 አንድ ቀን የኢዮብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት ተሰብስበው ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር፤
14 መልእክተኛም ወደ ኢዮብ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በሬዎች እያረሱ፣ አህዮችም በአጠገባቸው እየጋጡ ሳሉ፣
15 ሳባውያን ጥቃት አድርሰውባቸው ይዘዋቸው ሄዱ፤ አገልጋዮቹንም በሰይፍ ገደሉ። እኔም ብቻዬን አመለጥሁ፤ ልነግርህም መጣሁ።”
16 እርሱም እየተናገረ ሳለ፣ ሌላ መልእክተኛ መጥቶ፣ “የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወረደች፤ በጎችንና አገልጋዮችንም በላች፤ እኔም ብቻዬን አመለጥሁ፤ ልነግርህም መጣሁ” አለው።
17 እርሱም እየተናገረ ሳለ፣ ሌላ መልእክተኛ መጥቶ፣ “ከለዳውያን በሦስት ቡድን መጥተው ጥቃት አደረሱ፤ ግመሎችህንም ይዘው ሄዱ፤ አገልጋዮቹን በሰይፍ ገደሉ፤ እኔም ብቻዬን አመለጥሁ፤ ልነግርህም መጣሁ” አለው።
18 እርሱም እየተናገረ ሳለ፣ ሌላ መልእክተኛ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ተሰብስበው እየበሉና እየጠጡ ሳሉ፣
19 እነሆ፤ ታላቅ ዐውሎ ነፋስ ከምድረ በዳ መጣ፤ የቤቱንም አራት ማእዘናት መታ፤ እርሱም በልጆቹ ላይ ወድቆ ገደላቸው። እኔም ብቻዬን አመለጥሁ፤ ልነግርህም መጣሁ።”
20 ኢዮብም ተነሣ፤ ልብሱን ቀደደ፤ ራሱን ተላጨ፤ በምድርም ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤
21 እንዲህም አለ፤“ዕራቍቴን ከእናቴ ማሕፀን ወጣሁ፤ዕራቍቴንም እሄዳለሁ። እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም ቡሩክ ይሁን።”
22 በዚህ ሁሉ፣ ኢዮብ አልበደለም፤ በእግዚአብሔርም ላይ ክፉ አልተናገረም።