1 የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ይህም ማለት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ዘመነ መንግሥት በመጀመሪያው ዓመት፣ ስለ ይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ለኤርምያስ ቃል መጣለት፤
2 ስለዚህ ነቢዩ ኤርምያስ ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉ፣ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩትም ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፦
3 የይሁዳ ንጉሥ የአሞን ልጅ ኢዮስያስ ከነገሠበት ከዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሃያ ሦስት ዓመት ሙሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፤ ደጋግሜም ነገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም።
4 እግዚአብሔር አገልጋዮቹን ነቢያትን ሁሉ ደጋግሞ ወደ እናንተ ላከ፤ ሆኖም አልሰማችሁም፤ ትኵረትም አልሰጣችሁትም።