ኤርምያስ 27 NASV

የይሁዳ በናቡከደነፆር ሥር መውደቅ

1 በይሁዳ ንጉሥ፣ በኢዮስያስ ልጅ በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ላይ ይህ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ፤

2 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “የዕንጨት ቀንበር ሠርተህ በጠፍር ማነቆ አያይዘውና በዐንገትህ አስገባው፤

3 ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሴዴቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡት ሰዎች በኩል ለኤዶም፣ ለሞዓብ፣ ለአሞን፣ ለጢሮስና ለሲዶና ነገሥታት መልእክት ላክ።

4 ለጌቶቻቸውም እንዲያሳውቁ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ለጌቶቻችሁ ይህን ንገሯቸው፤

5 በታላቁ ኀይሌና በተዘረጋው ክንዴ ምድርን፣ በላይዋ የሚኖሩትን ሰዎችና እንስሳት ፈጥሬአለሁ፤ ለምወደውም እሰጣለሁ።

6 አሁንም እነዚህን አገሮች ሁሉ ለአገልጋዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣለሁ፤ የዱር አራዊት እንኳ እንዲገዙለት አደርጋለሁ።

7 የእርሱ አገር በተራው ለሌሎች እስከሚገዛበት ጊዜ ድረስ፣ ሕዝቦች ሁሉ ለእርሱ፣ ለልጁና ለልጅ ልጁ ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜ ብዙ ሕዝቦችና ታላላቅ ነገሥታት እርሱን ይገዙታል።

8 “ ‘ “ነገር ግን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደናፆር የማይገዛ፣ ዐንገቱንም ከቀንበሩ በታች ዝቅ የማያደርግ ማንኛውንም ሕዝብ ወይም መንግሥት በእጁ እስከማጠፋው ድረስ በሰይፍና በራብ፣ በመቅሠፍትም እቀጣዋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤

9 ስለዚህ፣ ‘የባቢሎንን ንጉሥ አታገለግሉም’ የሚሏችሁን ነቢያታችሁን፣ ሟርተኞቻችሁን፣ ሕልመኞቻችሁን፤ መናፍስት ጠሪዎቻችሁንና መተተኞቻቸሁን አትስሙ፤

10 ከምድራችሁ እንድትፈናቀሉ፣ እኔም እንዳሳድዳችሁና እንዳጠፋችሁ የሐሰት ትንቢት ይነግሯችኋልና።

11 ነገር ግን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች ዐንገቱን ዝቅ የሚያደርገውንና የሚያገለግለውን ማንኛውንም ሕዝብ በገዛ ምድሩ እንዲቀርና እያረሰም በዚያ እንዲኖር አደርገዋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።” ’ ”

12 ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስም ይህንኑ መልእክት እንዲህ ብዬ ነገርሁት፤ “አንገታችሁን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች ዝቅ አድርጉ፤ እርሱንና ሕዝቡን አገልግሉ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ።

13 አንተና ሕዝብህ፣ እግዚአብሔር ለባቢሎን ንጉሥ አልገዛም ያለውን ሕዝብ ባስጠነቀቀበት በሰይፍ፣ በራብና በመቅሠፍት ለምን ታልቃላችሁ?

14 ሐሰተኛ ትንቢት ስለሚነግሯችሁ፣ ‘የባቢሎንን ንጉሥ አታገለግሉም’ የሚሏችሁን ነቢያት አትስሙ፤

15 ‘እኔ አልላክኋቸውም’ ይላል እግዚአብሔር ‘የሐሰት ትንቢት በስሜ ይናገራሉ፤ ስለዚህ እናንተንና ትንቢት የሚናገሩላችሁን ነቢያት አሳድዳለሁ፤ እናንተም ትጠፋላችሁ።’ ”

16 እኔም ለካህናቱና ለዚህ ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አልሁ፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የእግዚአብሔር ቤት ዕቃ ከባቢሎን ቶሎ ይመለሳል’ የሚሏችሁን ነቢያት አትስሟቸው፤ የሚነግሯችሁ የሐሰት ትንቢት ነውና።

17 ስለዚህ እነርሱን መስማትትታችሁ ለባቢሎን ንጉሥ ተገዙ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ ባለመታዘዛችሁስ ይህቺ ከተማ ለምን ትፈራርስ?

18 እውነተኞች ነቢያት ከሆኑና በእርግጥ የእግዚአብሔር ቃል ካላቸው፣ በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት በኢየሩሳሌምም የቀሩት ዕቃዎች ወደ ባቢሎን እንዳይወሰዱ ወደ ሰራዊት ጌታ ወደ እግዚአብሔር እስቲ ይማልዱ!

19 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በዚህች ከተማ ስለ ቀሩት፦ ዐምዶች፣ ከናስ ስለ ተሠራው ትልቁ ገንዳ፣ ስለ ተንቀሳቃሽ ማስቀመጫዎችና ስለ ሌሎቹም ዕቃዎች እንዲህ ይላልና፤

20 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን፣ ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ መኳንንት ጋር ማርኮ ወደ ባቢሎን በወሰደ ጊዜ እነዚህ በከተማዪቱ የቀሩ ዕቃዎች ስለሆኑ፣

21 በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤተ መንግሥት በኢየሩሳሌምም ስለ ቀሩት ዕቃዎች፣ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

22 ‘ወደ ባቢሎን ይወሰዳሉ፤ እስከምጐበኛቸውም ቀን ድረስ በዚያ ይቀመጣሉ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘በዚያ ጊዜም እመልሳቸዋለሁ፤ ወደዚህም ስፍራ አመጣቸዋለሁ።’ ”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50 51 52